ዚምባብዌ በሮበርት ጋብሬል ሙጋቤ ስም ዩኒቨርሲቲ ልትገነባ ነው

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 4፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) ዚምባብዌ በ1 ቢሊየን ዶላር ወጪ የሮበርት ጋብሬል ሙጋቤ ዩኒቨርሲቲን ልትገነባ መሆኑ ተነግሯል፡፡

የሀገሪቱ የከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ጆናታን ሞዮ፥ ዩኒቨርሲቲው የሚገነባው የ93 ዓመቱ ፕሬዚዳንት ሙጋቤ ለትምህርት ላላቸው ቁርጥኝነት እና አርዓያነት ላለው አመራራቸው እውቅና ለመስጠት ነው ብለዋል፡፡

የሮበርት ጋብሬል ሙጋቤ ዩኒቨርሲቲ ትኩረቱን በሳይንስና ቴክሎጂ ላይ እንደሚያደርግ ነው የገለፁት፡፡

ዚምባብዌ በከፍተኛ የገንዘብ እጥረት ውስጥ ሆና ለዩኒቨርሲቲ ግንባታ የመደበችውን 1 ቢሊየን ዶላር ከየት ታገኛለች የሚለው ምላሽ ያላገኘ ጉዳይ ሆኗል፡፡

በሀገሪቱ ባለፈው የፈረንጆች ዓመት በተከሰተው ድርቅ ከ4 ሚሊየን በላይ ዜጎች ለምግብ እርዳታ ተዳርገው ነበር፡፡

ከዚህ ባለፈ ግን የዚምባብዌ ካቢኔ ከዋና ከተማዋ ሀራሬ 35 ርቀት ላይ በምትገኘው ማዞዌ፥ አዲሱን ዩኒቨርሲቲ ለመገንባት 800 ሚሊየን ዶላር ለመመደብ ተስማምቷል፡፡

ቀሪው 200 ሚሊየን ዶላር ገንዘብ ደግሞ በሮበርት ጋብሬል ሙጋቤ ዩኒቨርሲቲ ለሚከናወኑ የሳይንስና ፈጠራ ምርምሮች እንደሚውል ነው ሞዮ የተናገሩት፡፡

ሚኒስትሩ የገንዘብ ድጋፉ ምንጩ ከየት እንደሆነ ግን የጠቀሱት ነገር የለም፡፡

የዩኒቨርሲቲ ግንባታ እቅዱ የሙጋቤ ስልጣን እንዲያበቃ በሚፈልጉ ተቃዋሚዎች ከፍተኛ ተቃውሞ አስነስቷል፡፡

ሮበርት ጋብሬል ሙጋቤ በትምህርት ሰባት ዲግሪዎችን ሲያገኙ፥ 11 የክብር ዲግሪዎች እንደተሰጧቸው የሀገሪቱ የመንግስት መገናኛ ብዙሃን መረጃ ያሳያል፡፡

 

 

 

 

 

ምንጭ፡-ቢቢሲ