በአራት በግጭት ውስጥ ባሉ ሀገራት 20 ሚሊየን ሰዎች የረሃብ አደጋ ስጋት ተጋርጦባቸዋል - ተመድ

አዲስ አበባ ነሃሴ 4፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአራት በግጭት ውስጥ ያሉ የአፍሪካ ሀገራት ከ20 ሚሊየን በላይ ሰዎች የረሃብ አደጋ ስጋት ተጋርጦባቸዋል አለ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት።

የረሃብ ስጋቱ የተደቀነባቸው በየመን፣ ሶማሊያ፣ ደቡብ ሱዳን እና ናይጀሪያ የሚገኙ ዜጎች ናቸው።

የመንግስታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት የረሃብ አደጋ ስጋቱ በየሀገራቱ ከሚታየው ግጭት ጋር በቀጥታ ይገናኛል ብሏል።

ግጭቶቹ በንፁሃን ዜጎች ላይ እያደረሱት ያለው ጉዳት እጅግ አስከፊ መሆኑንም ጠቅሷል።

ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች የሰብአዊ እርዳታ ለማቅረብ የቀጠሉት ግጭቶች እንቅፋት ሆነዋል ያለው የፀጥታው ምክር ቤት፥ ይህም ዜጎችን ለረሃብ እያጋለጠ መሆኑን ጠቁሟል።

ምክር ቤቱ በተቃውሞ እና ግጭቶች ላይ እየተሳተፉ ያሉ የታጠቁ አካላት ንፁሃንን ሊያከብሩ እና ሊጠብቁ ይገባል ነው ያለው።

የመንግስታቱ ድርጅት አባል ድርጅቶችም የረሃብ አደጋ ስጋቱን ለመፍታት ቃላቸውን ጠብቀው ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቋል።

በድርጅቱ የአስቸኳይ ጊዜ ድጋፍ አስተባባሪ እና የሰብአዊ ድጋፍ ጉዳዮች አስተባባሪ ስቴፈን ብሪያን፥ ለአስቸኳይ ድጋፍ ከሚያስፈልገው 4 ነጥብ 9 በሊየን የአሜሪካ ዶላር ውስጥ እስካሁን ከለጋሾች የተሰበሰበው 2 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር ብቻ ነው።

ምንጭ፦ ፕረስ ቲቪ