ኤፍ ቢ አይ የቀድሞውን የትራምፕ የምርጫ ቅስቀሳ ሊቀመንበር ቤት በረበረ

አዲስ አበባ ፣ ነሃሴ 3 ፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) የአሜሪካ የምርመራ ቢሮ (ኤፍ ቢ አይ) የቀድሞውን የፕሬዚዳንት ትራምፕ የምርጫ ቅስቀሳ ሊቀ መንበር ፖል ማናፎርትን መኖሪያ ቤት በረበረ።

የምርመራ ቢሮው ሰራተኞች በግለሰቡ መኖሪያ ቤት በመገኘት ድንገተኛ ብርበራ አድርገዋል።

ብርበራው በ2016ቱ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ወቅት የሩሲያን ጣልቃ ገብነት ለማጣራት የሚካሄደው ምርመራ አንድ አካል ነው ተብሏል።

ሩሲያ በምርጫው ጣልቃ ገብታለች በሚል የቀረበውን ውንጀላ የሚያጣራ ልዩ ምክር ቤት ተቋቁሞ ጉዳዩን እያጣራ ይገኛል።

የዛሬው ድንገተኛ ብርበራም የዚህ ምርመራ አንድ አካል መሆኑ እየተነገረ ነው።

የምርመራ ቢሮው አባላት ባደረጉት ብርበራ የተወሰኑ የሰነድ መረጃዎችን አግኝተዋል ነው የተባለው።

ግለሰቡም የሩሲያን ጣልቃ ገብነት በሚያጣራው ልዩ ምክር ቤት መሪ ሮበርት ሚውለር ቃለ መጠይቅ እንደተደረገላቸው መረጃዎች ያሳያሉ።

ግለሰቡ ከዚህ ቀደም እጃቸው ላይ የሚገኙ የሰነድ እና የድምጽ ማስረጃዎችን ለሃገሪቱ ሴኔት እና ኮንግረስ አስረክበዋል።

የሰነድ ማስረጃዎቹ ፕሬዚዳንት ትራምፕ ከምርጫው ቀደም ብሎ በሰኔ ወር 2016 ከሩሲያዊው ጠበቃ ጋር ያደረጉትን ውይይት በተመለከተ ያሰፈሩትን ማስታወሻ የያዘ ነበር።

ግለሰቡ ከትራምፕ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ሊቀ መንበርነታቸው ከምርጫው ሶስት ወራት ቀደም ብለው ነበር የለቀቁት።

በወቅቱም በአሜሪካ እና ዩክሬን የክሬምሊንን ፍላጎት ለማንጸባረቅ ሚሊየን ዶላሮችን ተቀብለዋል የሚል ወቀሳ ቀርቦባቸው ነበር።

ከዚህ ባለፈም ከሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር ግንኙነት እንዳላቸው ከሚጠረጠሩ ሩሲያዊ ባለሃብት ጋር ተደራድረዋል የሚል ወቀሳም እንደቀረበባቸው ይታወሳል።

 

 

 


ምንጭ፦ ቢቢሲ