የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የዘጠኝ ወራት አፈፃፀም ተገመገመ

አዲስ አበባ፣ ሀምሌ 10፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ባለፉት ዘጠኝ ወራት ሲተገበር የቆየው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሃገሪቱን ሰላም በማስጠበቅ ውጤታማ ነበር ተባለ።

ብሄራዊ ኮማንድ ፖስቱ ባለፉት ዘጠኝ ወራት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈአፈጻፀም ሪፖርት አቅርቦ ውይይት ተደርጎበታል።

ኮማንድ ፖስቱ በቀረበው ሪፖርት ላይ ተወያይቶም መደምደሚያ ላይ መድረሱን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ብሄራዊ ኮማንድ ፖስት ሴክሬታሪያት አቶ ሲራጅ ፈጌሳ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ተናግረዋል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከታወጀበት ጊዜ አንስቶ በሀገሪቱ ሰላም እና ፀጥታ ሁኔታ መሻሻል አሳይቷል ያሉት የኮማንድ ፖስቱ ሴክሬታሪያት፥ አዋጁ ስኬታማ ነበር ብለዋል።

ህብረተሰቡ የሰላም ስጋት ይሆናሉ ያላቸውን አካላት አሳልፎ በመስጠት ረገድ ያደረገው ተሳትፎ በእጅጉ የጎላ መሆኑንም አንስተዋል።

በዘጠኝ ወሩ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ኮማንድ ፖስት የስራ ቆይታ የክልል የፀጥታ ሀይሎችን የማጠናከር ስራ ውጤት የተመዘገበበት ነው ብለዋል።

የክልል የፀጥታ አካላት ስራውን ከመረከባቸው በፊት ስልጠና ተሰጥቷቸዋል ያሉት አቶ ሲራጅ፥ ችግር እንዳለባቸው የተነሱትም እርማት እንዲወሰድባቸው መደረጉን ተናግረዋል።

በሁከት እና ግርግር ተሳትፈዋል በሚል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የዋሉ ዜጎች ፍትህ እንዲያገኙ እየተሰራ መሆኑንም ነው አቶ ሲራጅ የገለጹት።

የመሰረተ ልማት ስራዎችንና የኢንቨስትመንት ተቋማትን ደህንነት የማረጋገጥ፣ ሁከትና ብጥብጥን ለማስቀጠል የሚፈልጉትንና በተለያዩ የወንጀል ድርጊቶች የተሳተፉትን በቁጥጥር ስር የማዋል እንዲሁም ከህብረተሰቡ ለሚነሱ የመሰረተ ልማት ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት ወጣቱ ይበልጥ የስራ እድል እንዲያገኙ የተለያዩ ተግባራት መከናወናቸው ተነስቷል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የማራዘም ወይም ማንሳት ጉዳይም በሚመለከተው አካል ውሳኔ ይሰጥበታል ተብሏል።

 

 

 


በሰላማዊት ካሳ