የአማራ ክልል ምክር ቤት ለ2010 የ37 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር በጀት አፀደቀ

አዲስ አበባ፣ ሀምሌ 10፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአማራ ክልል ምክር ቤት ለ2010 በጀት አመት ከ37 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር በላይ በጀት አፅድቋል።

ምክር ቤቱ በዛሬው ውሎው በ2010 በጀት መግለጫ፣ ጥቅል በጀት ጣራ አመዳደብ እና የወረዳዎች እና ከተማ አስተዳደሮች የበጀት ድጎማ ቀመር ቀርቦ ውይይት ከተደረገ በኋላ በሙሉ ድምጽ አፅድቋል።

በዚህም መሰረት የ2010 በጀት ዓመት የልማት ስራዎች ማስፈጸሚያ የክልሉ ጠቅላላ በጀት 37 ቢሊየን 693 ሚሊየን 142 ሺህ 155 ብር ሆኖ ፀድቋል።

ይህ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ15 በመቶ ብልጫ አለው ተብሏል።

የ2009 በጀት ዓመት ለመንግስት ስራዎች ማስፈጸሚያ ተጨማሪ በጀት ለማስጸደቅ የወጣው አዋጅ ለምክር ቤቱ ቀርቦ በሙሉ ድምጽ ፀድቋል።

በተጨማሪም ምክር ቤቱ በዛሬ ውሎው የክልሉን የዋና ኦዲት ባለስልጣን፣ የክልል ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ሪፖርት እና የአማራ ክልል የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ማሻሻያ አዋጅ በመገምገም አጽድቋል።

የ2009 በጀት ዓመት የ11 ወራት የልማትና የመልካም አስተዳድር ዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርትም ለምክር ቤቱ ቀርቦ ሰፋ ያለ ውይይት ተደርጎበታል።

በውይይቱ ላይ የማጠቃለያ ሀሳብ የሰጡት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው፥ በክልሉ ተከስቶ የነበረው አለመረጋጋት በኢንቨስትመንትና በግብርናው ዘርፍ ላይ የጐላ ተፅዕኖ ባይደርስም በቱሪዝም ልማት ላይ ተፅዕኖ ማሳደሩን ገልጸዋል።

በመሆኑም በቀጣይ ለሰላም ዋጋ በመስጠትና የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ህገወጥ ተግባራትን የመከላከሉ ተግባር ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።

ባለፈው በጀት ዓመት በግብርናው ዘርፍ ዕድገት የታየበት ዘመን ቢሆንም ከዕድገትና ከትራንስፎርሜሽኑ ዕቅድ አኳያ የሚቀር ስራ አለ ያሉት ር:ሰ መስተዳደሩ፥ በዓመቱ በትራንስፖርትና በግዥ መጓተት ምክንያት የግብርና ግብአት አቅርቦት እጥረት መከሰቱ ለዘርፉ ትልቅ ማነቆ መሆኑን ገልጸዋል።

በክልሉ የተከሰተውን ተምች አርሶ አደሮች በቡድን በመደራጀት መከላከል እንዳለባቸውም ጠይቀዋል።

በጣና ሀይቅ ላይ የተፈጠረው እንቦጭ የተባለው መጤ አረምን ሙሉ በሙሉ ለማስወገድ አስቸጋሪ ሁኗል ያሉት አቶ ገዱ፥ በመሆኑም ሁሉም የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት በመስጠት እንዲረባረቡ ጥሪ አቅርበዋል።

የምክር ቤቱ 5ኛ ዙር 2ኛ ዓመት የስራ ዘመን 7ኛ መደበኛ ጉባዔ የቀረበውን ሪፖርት በሙሉ ድምጽ በማፅደቅ መጠናቀቁን የክልሉ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት አስታውቋል።