በደቡብ ክልል በተዘዋዋሪ ፈንዱ ከ80 ሺህ በላይ ወጣቶች የስራ እድል ተፈጥሮላቸዋል

አዲስ አበባ፣ ሀምሌ 10፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በደቡብ ክልል በ2009 በጀት አመት በተዘዋዋሪ ፈንዱ የስራ እድል ይፈጠርላቸዋል ከተባሉ 169 ሺህ ወጣቶች ከግማሽ በላዩ ወደ ስራ ማስገባት ተችሏል።

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አቶ መለስ አለሙ፥ ክልሉ ከተዘዋዋሪ ፈንዱ 1 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር እንደተበጀት አስታውሰው፥ በዚህ በጀት አመት ከ169 ሺህ በላይ ወጣቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዶ እንደነበር ገልፀዋል።

ይሁን እንጂ ማሳካት የተቻለው የእቅዱን ከ50 በመቶ ያልበለጠ ነው።

ለዚህም ከፌደራል መንግስት የተዘዋዋሪ ፈንዱ በሚፈለገው ጊዜ አለመለቀቅና የዝግጅት ሂደቱ መጓተትን በምክንያትነት አንስተዋል።

አሁን ችግሩን ከመለየት ባለፈ የመፍታት ስራ እየተሰራ መሆኑን ያነሱት አቶ መለስ፥ የቅድመ ዝግጅት ስራው በሚፈለገው ደረጃ ላይ የሚገኝ በመሆኑ ወጣቱን በተከታታይ ወደ ስራ ለማስገባት የሚቻልበት አቅም ተፈጥሯል ብለዋል።

በገጠር የተዘጋጀው 2 ሺህ 276 ሄክታር መሬትና በከተማ 903 ሺህ ካሬ መሬት እንዲሁም 405 ሼዶች ለወጣቱ ቀድመው መዘጋጀታቸውንም ለዚሁ በማሳያነት አንስተዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ቀደም ሲል የተለዩ 16 ሺህ ውጤት ተኮር ቢዝነስ ፕላኖችን ወደ ስራ ማስገባት መቻሉን ጠቁመዋል።

አዋጪ የሆኑ ከ20 በላይ የቢዝነስ ፕላኖችም በተለያዩ ባለሙያዎች ተጠንተው በሁለት ወራት ውስጥ ስራ ላይ ለማዋል ይሰራል ነው ያሉት።

የወጣቱ ፍላጎትና ዝንባሌ የሚስተናገድበት ነው የተባለው ቢዝነስ ፕላን በተለይ የማምረቻና የግብርናው ዘርፍን ትኩረት ያደረጉ ናቸው።

በክልሉ በተከናወነው የስራ አጥ ልየታ ከ6 ሺህ በላይ የዲግሪ ምሩቃንና ከ30 ሺህ በላይ የቴክኒክና ሙያ ተመራቂዎችም ተለይተው በቅድሚያ ወደ ስራ እንዲገቡ ከተደረጉት ውስጥ ይገኙበታል ብለዋል።

የእድሉ ተጠቃሚ ሆነው አሁን ወደ ስራ የገቡና እየገቡ ያሉ ወጣቶች አስፈላጊውን ዝግጅት አድርገው ወደ ስራ መግባታቸውን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል።

በክልሉ ከተዘዋዋሩ ፈንዱ ውጪ የሚስተናገዱ በገጠር 400 ሺህ በከተማ ደግሞ 280 ሺህ ዜጎች በመደበኛው የስራ እድል ፈጠራው እየተስተናገዱ መሆኑ ተገልጿል።

 

 

 

በሀይለኢየሱስ ስዩም