የካሜሮን ጦር ጀልባ ሰጥማ ከ30 በላይ ሰዎች ጠፍተዋል

አዲስ አበባ፣ ሀምሌ 10፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) አሸባሪው ቦኮሃራምን ለመዋጋት በካሜሮንና ናይጀሪያ ድንበር ላይ ተልዕኮውን እየተወጣ ያለው የካሜሮን ጦር ይጓዝበት የነበረችው ጀልባ ሰጥማ 34 ሰዎች ያሉበት አልታወቀም።

የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ፅህፈት ቤት በጀልባዋ ውስጥ 37 የጦሩ አባላት እንደነበሩ ገልጿል።

ጀልባዋ በካሜሮን ባህር ዳርቻ አካባቢ በምትገኘው ባካሲ ለሚገነባው የጦር ሰፈር ሙሉ ቁሳቁስ የምታቀርብ ነበረች።

አደጋው የደረሰው በሰሜን ካሜሮን የባህር ዳርቻ በሚገኘው ደቡንሻ አካባቢ ነው።

የአደጋው መንስኤ እየተጣራ ሲሆን፥ ሃይለኛ ውሽንፍር ተከስቶ እንደነበር ተገልጿል።

ይሁንና አሁንም የአደጋውን መንስኤ እያጣራ መሆኑን የሀገሪቱ መንግስት አስታውቋል።

ቦኮሃራም በካሜሮን ላይ ተደጋጋሚ ጥቃት እያደረሰ ሲሆን፥ ሀገሪቱም አሸባሪ ቡድኑን ለመዋጋት የሚደረገውን ጥረት አጠናከራ መቀጠሏን ገልጻለች።

ሀገሪቷ ቦኮሃራምን ለመዋጋት በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ወታደርን ወደ ሰሜን የሀገሪቱ ከፍል ያሰማራች ሲሆን፥ ውጊያውንም አጠናክራ መቀጠሏ ተነግሯል።

አሸባሪው ቡድንም እስካሁን ከ20 ሺህ በላይ ዜጎችን ገድሎ ከ2 ነጥብ 7 ሚሊየን በላይ የሚሆኑት ደግሞ እንዲፈናቀሉ አድርጓል።

 

 


ምንጭ፦ አልጀዚራ