ጨፌ ኦሮሚያ ለ2010 55 ነጥብ 81 ቢሊየን ብር በጀት አፀደቀ

አዲስ አበባ፣ ሀምሌ 10፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የጨፌ ኦሮሚያ 2ኛ ዓመት 6ኛ መደበኛ ጉባዔ ከ55 ነጥብ 81 ቢሊየን ብር በላይ ሆኖ የተዘጋጀውን የክልሉን መንግስት የ2010 ዓ.ም በጀት አፀደቀ።

በጀቱ ካለፈው አመት ጋር ሲነጻጸር የ9 ቢሊየን ብር ብልጫ አለው።

በጀቱ 10 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር በላይ ለክልሉ ተዘዋዋሪ በጀት፣ 13 ነጥብ 2 ቢሊየን ለካፒታል በጀት፣ ከ31 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር በላይ ለከተማ እና ወረዳ በጀት እንዲሁም 500 ሚሊየን ብር በላይ ደግሞ ለክልሉ የመጠባበቂያ በጀት የተመደበ መሆኑም ተገልጿል።

ገንዘቡም ከፌደራል መንግስት ድጎማ እና ከክልሉ መደበኛ ገቢ የሚገኝ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፥ ለፕሮጀክቶች ግንባታ ደግሞ ከውጭ የሚገኝ ድጋፍ ነው ተብሏል።

በተያያዘ የጨፌ ኦሮሚያ ጽህፈት ቤት የ2009 የስራ አፈጻጸምን አድምጧል።

ከዚህ በተጨማሪም ጨፌው የማህበራት የመስኖ አጠቃቀም ረቂቅ አዋጅን መርምሮ አጽድቋል።

ረቂቅ አዋጁ የክልሉ የመስኖ ውሃ አጠቃቀም የህግ ማእቀፍ እንዲኖረው እና በግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ የሚኖረውን ሚና ከፍ ለማድረግ እንዲሁም በመስኖ ውሃ አጠቃቀም ጋር የሚስተዋሉ ግጭቶችን ለመቅረፍ የወጣ መሆኑ ተገልጿል።

ጨፌው የክልሉን የአስፈጻሚ አካላት ለማደራጀት እንዲሁም ሀላፊነት እና የስራ ድርሻን ለመወሰን የወጣውን ረቂቅ አዋጅም አጽድቋል።

ረቂቅ አዋጁ ከዚህ ቀደም ተጠሪነቱ ለክልሉ ርዕሰ መስተዳደር የነበረውን የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን በክልሉ ፀጥታና አስተዳደር ቢሮ ስር እንዲሆን ይደነግጋል።

ዋና አላማውም በየእለቱ የሚፈፀሙ ወንጀሎችን በቅርበት ለመከታተል እና መፍትሄ ለመስጠት እንዲሁም በፖሊስ እና በፍትህ ቢሮ መካከል ያለውን የአሰራር ክፍተት ለመቅረፍ መሆኑም ነው የተገለፀው።

ጨፌው የተለያዩ ሹመቶችንም አፅድቋል። በዚህም መሰረት፦

የክልሉ ትምህርት ቢሮ ሀላፊ - ዶክተር ቶላ በሪሶ

የክልሉ የመንገዶች ባለስልጣን ስራ አስኪያጅ - ዶክተር ሀብታሙ ኢተፋ ገለታ

የወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ ሀላፊ - አቶ ሞቱማ ተመስገን 

የጨፌው ፅህፈት ቤት ሀላፊ - ሰማን አባ ጎጃም እንዲሆኑ ተሹመዋል።

ለከፍተኛ ፍርድ ቤት አራት፣ ለወረዳ ፍርድ ቤት  ደግሞ 194 ዳኞች ሹመትንም ጨፌው አፅድቋል።

 

 

በሰርካለም ጌታቸው