በአርባምንጭ ከተማ ህንጻ ተደርምሶ የ4 ሰዎች ህይወት አለፈ

አዲስ አበባ፣ ሀምሌ 10፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአርባምንጭ ከተማ ባለ አራት ፎቅ ህንጻ ተደርምሶ የአራት ሰዎች ህይወት ሲያልፍ በ11 ሰዎች ላይ ደግሞ ጉዳት መድረሱን ፖሊስ አስታወቀ።

የከተማው ፖሊስ አዛዥ ምክትል ኮማንደር ተመስገን አንጁሎ፥ እንደገለፁት አደጋው ትናንት ጠዋት ላይ የደረሰው በከተማው ዓባያ ክፍለ ከተማ ኩልፎ ቀበሌ ሚካኤል ተብሎ በሚጠራው መንደር ነው።

በመንደሩ ንብረትነቱ የአቶ ወልደሰንበት ጋጋ የሆነ ባለአራት ፎቅ መኝታ ቤት ተደርምሶም በመኝታ ቤቱ አልጋ ይዘው የነበሩ የአራት ሰዎች ህይወት አልፏል፡፡

ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ደግሞ በአርባምንጭ ሆስፒታል ህክምና እየተደረገላቸው መሆኑን ምክትል ኮማንደሩ አመልክተዋል፡፡

የአርባምንጭ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ኤዞ ኤማቆ በበኩላቸው፥ ግለሰቡ ህንፃውን የግንባታ ፈቃድ ሳያገኝ እየገነባ መሆኑ በመረጃ ተደርሶበት በህግ መጠየቁን ገልጸዋል።

ደረጃውን ሳይጠብቅ በድብቅ ማታ ማታ ግንባታውን በማካሄድ በህገ ወጥ መንገድ የመኝታ ቤት ኪራይ አገልግሎት ሲሰጥ መቆየቱንም ጠቅሰዋል።

በዚህ ህገ ወጥ ተግባሩ ቀደም ሲል ክስ ተመስርቶበት በህግ ሂደት ላይ እያለ አደጋው መድረሱን ጠቁመዋል።

ግለሰቡ በአሁኑ ወቅት በህግ ቁጥጥር ስር መዋሉንም አመልክተዋል።

ምንጭ፦ ኢዜአ