ደቡብ ኮሪያ በወታደራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከሰሜን ኮሪያ ጋር የመነጋገር እቅድ አለኝ አለች

አዲስ አበባ፣ ሀምሌ 10፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ደቡብ ኮሪያ በወታደራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከሰሜን ኮሪያ ጋር ለመነጋገር እቅድ እንዳላት አስታውቃለች።

የደቡብ ኮሪያ ከፍተኛ ባለስልጣናት፥ የውይይቱ አላማ በሁለቱ ሀገራት ድንበር አካባቢ የሚስተዋለውን ወታደራዊ ውጥረት ለማርገብ እንደሆነ ተናግረዋል።

የደቡብ ኮሪያ የመከላከያ ሚኒስትር ዴኤታ ሱህ ቾኦሱክ መግለጫ፥ ወታደራዊ ውይይቱ በሰሜን ኮሪያ ፓንሙጆን ቶንጊልጋክ በተባለ ህንጻ ውስጥ ነው የሚካሄደው።

ውይይቱም አርብ ሀምሌ 14 ለማድረግ ታቅዷል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፥ “ከሰሜን ኮሪያ አዎንታዊ ምላሽ እንጠብቃለን” ሲሉም ተናግረዋል።

በቅርቡ ወደ ስልጣን የመጡት የደቡብ ኮሪያ ፕሬዚዳንት ሙን ጃይኢን፥ ሁለቱን ኮሪያዎች የማቀራራብ ፍላጎት እንዳላቸው መግለፃቸው ይታወሳል።

ፕሬዚዳንቱ በቅርቡ በበርሊን ባደረጉት ንግግርም “ከሰሜን ኮሪያ ጋር ለመነጋጋር ያለን ፍላጎት ከመቸውም ጊዜ በላይ የጨመረ ነው” ያሉ ሲሆን፥ በሁለቱ ሀገራት መካካልም የሰላም ስምምነት እንዲፈረም ጥሪ አቅርበዋል።

በሀገራቱ መካካል ሊደረግ የታሰበው ውይይትም የፒዮንግያንግ የኒውክሌር መርሃ ግብር እንዲቆም ለሚፈልጉ አካላት መልካም ነገር ነው ብለዋል።

የሁለቱ ሀገራት ውይይት በእቅዱ መሰረት የሚሄድ ከሆነም እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጣር ከ2015 ወዲህ በሁለቱ ሀገራት መካከል በከፍተኛ ባለስልጣናት ደረጃ የተካሄደ የመጀመሪያው ውይይት እንደሚሆነም ተነግሯል።

ምንጭ፦ ቢቢሲ