በሴኔጋል በደረሰ የስታዲየም መደርመስ አደጋ ስምንት ሰዎች ሞቱ

አዲስ አበባ ፣ ሃምሌ 9 ፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) በሴኔጋል የእግር ኳስ መጫወቻ ስታዲየም በደረሰ የመደርመስ አደጋ ስምንት ሰዎች መሞታቸው ተነገረ።

አደጋው በዋና ከተማዋ ዳካር በሚገኘው የዴምባ ዲዮፕ ስታዲየም በተደረገ የአመቱ የሴኔጋል ሊግ የዋንጫ ጨዋታ ላይ የደረሰ ነው ተብሏል።

በወቅቱ ስታድ ምቦር እና ዩኒየን ስፖርቲቭ ኦካም የተባሉ ቡድኖች የፍጻሜ ጨዋታቸውን እያደረጉ ነበር።

የጨዋታው መደበኛ ዘጠና ደቂቃ አንድ አቻ ከተለያዩ በኋላ ቡድኖች ወደ ጭማሪ ሰዓት አምርተዋል።

በዚህም በጭማሪው ሰዓት ስታድ ምቦር የተባለው ቡድን ጎል አስቆጥሮ ጨዋታው በምቦር 2 ለ 1 አሸናፊነት ይጠናቀቃል።

ይሁን እንጅ የጨዋታውን መጠናቀቅ ከሚያበስረው የእለቱ የመሃል ዳኛ ፊሽካ በኋላ ስታዲየሙ ውስጥ ረብሻ ይነሳል።

በዚህ ረብሻ ሳቢያም ደጋፊዎች ከፖሊስ አባላት ጋር ተጋጭተዋል፥ ትንሽ ቆይቶም ደጋፊዎች የነበሩበት የስታዲየሙ አንድ ክፍል ግድግዳ ተደርምሷል።

በዚህ ሳቢያም የስምንት ሰዎች ህይዎት ወዲያውኑ ሲያልፍ 49 ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸው ነው የተነገረው።

ከጨዋታው በኋላ የተፈጠረው አጋጣሚ ለዚህ ምክንያት መሆኑን ከአደጋው የተረፉ ታዳሚዎች ተናግረዋል።

የሃገሪቱ መንግስትም ሊያካሂደው የነበረውን የሃገሪቱን ምርጫ አደጋውን ተከትሎ መሰረዙ ተሰምቷል።

 

 

ምንጭ፦ ቢቢሲ