በኢትዮጵያ ሶማሌ የሕፃናት ስርዓተ ምግብን ለማሻሻል የተቀናጀ ድጋፍ ያስፈልጋል ተባለ

አዲስ አበባ ፣ ሃምሌ 9 ፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል የሕፃናትን ስርዓተ ምግብ ለማሻሻልና ችግሮችን ለማቃለል የሁሉም ባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ቀዳማዊት እመቤት ወይዘሮ ሮማን ተስፋዬ ተናገሩ፡፡

በኢትዮጵያ ሶማሌ ሁለተኛው ክልላዊ የሕፃናት ስርዓተ ምግብ እና የመጀመሪያው አንድ ሺህ ቀናት የሕፃናት ሥርዓተ ምግብ የሚለው ፕሮግራም በቀዳማዊት እመቤት ሮማን ተስፋዬ እና በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አብዲ መሐሙድ በይፋ ተጀምሯል።

ቀዳማዊት እመቤት ሮማን ተስፋዬ በስነ ስርዓቱ ላይ እንደተናገሩት፥ ጤናማና በሁሉም የልማት ስራዎች በብቃት የሚሳተፍ ዜጋ ለማፍራት የህፃናት ስርዓተ ምግብ መተግበር ጠቀሜታው የጎላ ነው።

በተለይ እናቶች ከእርግዝና ወቅት ጀምሮ ህፃናት ሁለት ዓመት እስከሚሞላቸው ድረስ በንጥረ ነገር የበለፀገ ምግብ እንዲያገኙ በማድረግ በአዕምሮ የበለፀገና የተስተካከለ እድገት እንዲኖራቸው ማድረግ ይቻላል ብለዋል።

እንደ ወይዘሮ ሮማን ገለፃ የሥርዓተ ምግብ ችግር በሕፃናት ላይ ያለ ዕድሜ መቀጨጭን እና ሌሎች የጤና ችግሮችን ያስከትላል ።

በክልሉ የሚገኙ ህፃናት ከስርዓተ ምግብ መጓደል ጋር ተያይዞ የሚደርስባቸውን የጤና ችግሮች ለማቃለል የሁሉም አካላት የተቀናጀ ጥረትና ድጋፍ ያስፈልጋል ተብሏል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አብዲ መሐሙድ በበኩላቸው፥ የስርዓተ ምግብ ፕሮግራሙ የህፃናቱን ትምህርት የመቀበል አቅምን በማሳደግ፣ የአዕምሮ ብቃታቸውንና የአካል ጥንካሬያቸው የሚያሻሽሉ ስራዎች የተካተቱበት መሆኑን ተናግረዋል።

በክልሉ ህፃናት ላይ የሚታየውን የምግብ አለመመጣጠን ችግር ለማቃለልና የህብረተሰቡን የአመጋገብ ሥርዓት ለማሻሻል ፕሮግራሙ ወሳኝ ድርሻ እንዳለውም ገልጸዋል፡፡

ፕሮግራሙን ተግባራዊ ለማድረግ ከክልሉ ጤና ቢሮ ጋር በመተባበር የሚሰሩ የክልሉ ትምህርት ቢሮ፣ የሴቶችና ሕፃናት ጉዳይ፣ የውሃ ሀብት ልማት ቢሮን ጨምሮ 11 ሴክተር መስሪያ ቤቶች መለየታቸውንም ጠቅሰዋል።

በሥነ ስርዓቱ ላይ የክልሉ ስራ ኃላፊዎች የወረዳ ጤና ጽህፈት ቤት አስተባባሪዎች እና በጤናው ሴክተር አጋር ድርጅት ተወካዮች መሳተፋቸውን ኢዜአ ዘግቧል።