በአማራ ክልል በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በግብርና ምርታማነት የተሻለ ውጤት ተመዝግቧል- አቶ ገዱ አንዳርጋቸው

አዲስ አበባ፣ ሃምሌ 8፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) ትናንት የተጀመረው የአማራ ክልል ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤ በዛሬው ውሎው የክልሉን የ2009 የአፈጻጸም ሪፖርት አድምጧል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ባቀረቡት ሪፖርት በግብርናው ዘርፍ ምርታማነት በተጠናቀቀው በጀት የተሻለ ውጤት መመዝገቡን ነው ያብራሩት።

amhara_council.jpg

በዚህም በ2008/2009 የምርት ዘመን 95 ነጥብ 2 ሚሊየን ኩንታል መርት መገኘቱን የገለጹ ሲሆን፥ ምርቱ ከቀዳሚው ዓመት የ7 ነጥብ 8 ሚሊየን ኩንታል ብልጫ ነበረው ብለዋል።

ያለአግባብ ይዞታቸውን አጥተው የነበሩ 1 ሺህ 835 አርሶ አደሮች ይዞታቸው እንደተመለሰላቸውም በሪፖርቱ አቅርበዋል፡፡

ህዝቡ ለሚያነሳቸው የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት ከአመራር ግምገማ አንስቶ በየደረጃው የተወሰዱ እርምጃዎችና ማስተካከያዎች ለውጥ እያመጡ መሆኑም በጉባኤው ተመልክቷል።

በጉባኤው በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በኢኮኖሚ፣ በገጠር ልማት፣ በንግድ ስርዓት፣ በመሰረተ ልማት እና በመልካም አስተዳደር ዘርፎች የተሰሩ ስራዎች አፈጻጸም ቀርቧል፡፡

የምክር ቤቱ አባላት ሪፖርቱን መሰረት ያደረጉ አስተያየት እና ጥያቄዎች ያቀረቡ ሲሆን በቀጣይ ሊሻሻሉ የሚገባቸው ተግባራት ትኩረት እንዲሰጣቸው አሳስበዋል፡፡

ምክር ቤቱ በቀጣይ ቀናት ውሎው በቀጣይ በጀት ዓመት እቅድ እና በሌሎች አጀንዳዎች ላይ ይመክራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

 

 

 

ሙሉጌታ ደሴ