በኦሮሚያ ክልል በፍትህ ዘርፍ የስነ ምግባር ጉድለት የፈጸሙ ሃላፊዎች ላይ እርምጃ ተወሰደ

አዲስ አበባ፣ ሃምሌ 7፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል በያዝነው አመት በፍትህ ዘርፍ ሃላፊነት ላይ የነበሩ ከ300 በላይ ባለስልጣናት ላይ እርምጃ ተወስዷል።

የፍትህ ዘርፍ ከፍተኛ የመልካም አስተዳደር እሮሮ የሚሰማበት ሲሆን በገንዘብ ከመሸጥ ጀምሮ ባለጉዳይን እስከ ማጉላላት ህዝብን ያማረረ ድርጊት የሚፈፀምበት ነው።

ይሄ እሮሮ የፍትህ ዘርፉ አካል በሆኑ ፍርድ ቤቶ፤ ፖሊስ ጣቢያዎች፣ አቃብያን ህግ እና ዳኞች ላይ የሚያርፍ ነው።

በጨፌ ኦሮሚያ የአስተዳደር እና ህግ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ኢሳ ቦሩ እንደሚናገሩት፥ ዘርፉ ስልጣንን ያለ አግባብ የመጠቀም ህገ ወጥ ድርጊት የሚፈፀምበት እስከ መሆን ደርሷል።

የክልሉ መንግስት በዘርፉ ያሉትን ችግሮች በጥናትም በህዝብ ውይይትም ከለየ በኋላ፥ የማጥራት እርምጃ የተወሰደ ሲሆን እርምጃው ከክልል እስከ ወረዳ የደረሰ መሆኑንም ያነሳሉ።

የክልሉ መንግስት ከጥልቅ ተሃድሶው በኋላ እየወሰደ ባለው እርምጃ፥ ህዝቡን ለምሬት የዳረጉ የፍትህ ጽህፈት ቤት እና የፖሊስ መምሪያ አመራሮች ከሃላፊነታቸው እንዲነሱ መደረጉንም ገልፅዋል።

የክልሉ የዳኞች አስተዳደር ጉባኤም የስነ ምግባር ጉድለት ፈጽመዋል ባላቸው አምስት ዳኞች ላይ ከዳኝነት እንዲነሱ ለጨፌ ኦሮሚያ የውሳኔ ሃሳብ አቅርቧል።

ከዚህ በተጨማሪም በዞንና በወረዳ ደረጃ 175 አመራሮች እና የስራ ሂደት መሪዎች ከሃላፊነታቸው እንዲነሱ ተደርጓል፡፡

በፖሊስ ኮሚሽን በኩልም የህዝቡ የፍትህ ስርዓት ቅሬታ መነሾ ናቸው የተባሉ 128 አመራሮች ከሀላፊነታቸው ሲነሱ፥ 64ቱ ደግሞ ከደረጃቸው ዝቅ እንዲሉ ተደርጓል ነው የተባለው።

የአቅም ውስንነት የታየባቸው 607 የኮሚሽኑ ሰራተኞች አቅማቸው በሚፈቅደው ስፍራ እንዲመደቡ መደረጉንም አቶ ኢሳ አመላክተዋል።

ፍርድ ቤቶች ላይ ያለውን ችግር ለመፍታትም አቃብያን ህጎች እና መርማሪ ፖሊሶች ላይ የሚደረገውን ቁጥጥር በማጥበቅ፥ ጉዳዮች በፍጥነት ፍርድ ቤት ቀርበው ውሳኔ እንዲያገኙ ማድረግ እንደሚገባም አሳስበዋል።

ከዚህ ባለፈም የስነ ምግባር ጥሰት መፈፀማቸው በክልሉ የዳኞች አስተዳደር ጉባኤ የተረጋገጠባቸው አምስት ዳኞች ከሃላፊነታቸው እንዲነሱ የሚያደርግ የውሳኔ ሃሳብ ለጨፌው ይቀርባልም ብለዋል።

ጨፌው ውሳኔውን ካፀደቀም ዳኞቹ ከስራቸው የሚሰናበቱ ይሆናል።

 

 

 

 

በሰርካለም ጌታቸው