በኤርትራ የሚገኙ ተቃዋሚ ቡድኖች ዓላማ የልማት ፕሮጀክቶችን ማደናቀፍ ነው - የቤህነን ቡድን አመራርና አባላት

አዲስ አበባ ፣ ሃምሌ 7 ፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) በኤርትራ የሚገኙ ተቃዋሚ ቡድኖች ዓላማ በኢትዮጵያ የሚከናወኑ የልማት ፕሮጀክቶችን ማደናቀፍ መሆኑን የአመጽ ተግባራቸውን በመተው ወደ ሃገራቸው የተመለሱ ራሱን የቤኒሻንጉል ህዝቦች ነፃነት ንቅናቄ /ቤህነን/ ብሎ የሚጠራው ቡድን አመራርና አባላት ገለፁ፡፡

የቤህነን መሪ አቶ አብዱላሃብ መሃዲ እንደተናገሩት፥ አርበኞች ግንቦት ሰባት በማለት ራሱን የሚጠራው ድርጅት ጨምሮ በኤርትራ የሚገኙ ቡድኖች በጋራ ባደረጉት ውይይት በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ ጥቃት ለማድረስ ተስማምተዋል፡፡

ይህን ሀሳብ በመቃወምም እሳቸውን ጨምሮ 95 የድርጅቱን አመራሮችና አባላትን የያዘ ቡድን ሰሞኑን ወደ ሃገሩ መግባቱንም ገልፀዋል።

ወደ አገራቸው የገቡት የድርጅቱ አመራሮችና አባላቱ የአገሪቱ ሰላም ተጠብቆ እየተካሄደ ያሉት የልማት ፕሮጀክቶች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን አቶ አብዱላሃብ ተናግረዋል፡፡

ድርጅቱን ከተቀላቀለ 10 ዓመታት ያስቆጠረው ሻምበል ሃሊፋ አህመድ በበኩሉ፥ ኤርትራ እያሉ ኢትዮጵያ እየተበታተነች የምትገኝና አቅም የሌላት ሃገር መሆኗ እንደሚነገራቸው ገልጿል፡፡

''የልማት ፕሮጀክቶች ላይ ጥቃት ለመፈፀም የሚያቅድ ኃይል ለህዝብ የቆመ አይደለም'' ያለው ሻምበል ሃሊፋ፥ በኤርትራ የሚገኙ ተቃዋሚ ቡድኖች ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ ጥቃት ለማድረስ ማሰባቸውን በመቃወም ከቡድኑ ጋር ሊመለስ መቻሉን ተናግሯል፡፡

ሌላው የድርጅቱ አባል የነበረውና ወደ ሃገሩ የተመለሰው አልሃጂ አፈንጂ፥ ''ወደፊት የተሻለ የህዝብ ኑሮ አመጣለው በማለት የሚታገል ድርጅት በህዝቦች የጋራ ትብብር የሚሰራን ሃገራዊ ፕሮጀክት የማፍረስ ዓለማ ሊኖረው አይችልም'' ብሏል፡፡

በመሆኑም በኤርትራ የሚገኙ ተቃዋሚ ኃይሎች ህዝባዊ ዓላማ የሌላቸው በመሆኑ ወደ ሃገሩ መመለሱን ጠቁሟል።

የተመሱት የቡድኑ አባላት የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሌሎች ትላልቅ አገራዊ ኘሮጀክቶች እስኪጠናቀቁ ድረስ ከመላው ኢትዮጵያውያን ጋር በመሆን በሠላም ማስጠበቁም ሆነ በልማት ተሳትፎ ለማድረግ መወሰናቸውንም ገልጿል፡፡

 

 

 

ምንጭ፦ ኢዜአ