የእናቶች ሞትን በመቀነስ ኢትዮጵያ በአፍሪካ መሪ ሆናለች

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 28፣ 2006 (ኤፍ.ቢ.ሲ.) ሴቭ ዘ ቺልድረን በየዓመቱ ይፋ በሚያደርገው ሪፖርቱ እንደጠቆመው ኢትዮጵያ የእናቶች ሞት ቁጥር በሁለት ሶስተኛ በመቀነስ ከአፍሪካ ቀዳሚ አገር ሆናለች።

 

የድርጅቱ ሪፖርት እንደሚያመለክተው፥ በአውሮፓውያኑ 2000 ላይ በአገሪቱ ከ24 እናቶች መካከል አንዷ ከወሊድ ጋር በተያያዘ ህይወቷ ያልፍ ነበር።

በአሁኑ ወቅት ግን ከ67 እናቶች መካከል አንዷ ከወሊድ ጋር በተያያዘ ለሞት እንደምትዳረግ ነው ሪፖርቱ ያመለከተው።
ኢትዮጵያ ቁጥሩ ሰፊ የሆነ የጤና ኤክስቴንሽ ባለሙያ ማሰማራቷና የልጃገረዶች ትምህርትን በማስፋፋቷ ውጤቱን ማግኘቷ ተገልጿል።

በመላው አገሪቱ ከ30 ሺህ የሚበልጡ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች ለህብረተሰቡ በሽታን የመከላከልና ማከም አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ።

በዚህም አገልግሎት ከወሊድ በፊት ለእናቶች የሚሰጠው ክብካቤ ስፋት ከ27 በመቶ ተነስቶ አሁን ከ42 በመቶ በልጧል።