የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የ2006/07 የመኸር የዝግጅት ስራ በተቀመጠለት አቅጣጫ እየተከናወነ መሆኑን አመለከተ

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 3 ፣ 2006 (ኤፍ.ቢ.ሲ.) የኢትዮጵያ አብዮታዊ ዴሞክራሲ ህዝቦች ግንባር ኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የ2006/07 የመኸር የዝግጅት ስራ በተቀመጠለት አቅጣጫ እየተከናወነ መሆኑን አመለከተ።

 

ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ትናንት ማምሻውን ባካሄደው መደበኛ ስብሰባው በ2006/07 የመኸር ዝግጅት ስራ እና በሌሎች አጀንዳዎች ላይ ተወያይቶ አቅጣጫዎች ማስቀመጡን የኢህአዴግ ምክር ቤት ፅሕፈት ቤት በላከው መግለጫ አስታወቋል።

ኮሚቴው የ2006/07 የመኸር ስራ በመስኩ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የመጨረሻ ዘመን በመሆኑ ፥ የዕቅድ ዝግጅቱ በዋናዋና የምግብ ሰብሎች ፣ በኤክስፖርት ምርቶችና በኢንዱስትሪ ግብአቶች ላይ እንዲሆን ያስቀመጠው አቅጣጫ በትክክል እየተከናነወ መሆኑን ገምግሟል።

በምርጥ ዘርና ማዳበሪያ አቅርቦት በኩል በዋናዋና ሰብሎች የ20 በመቶ ዕድገት ለማስመዝግብ የተቀመጠውን ግብ ለማሳካት የሚያስችል አቅርቦትና ስርጭት መኖሩን አረጋግጧል።

የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ትኩረት ሰጥቶ የተወያየበት ሌላው ጉዳይ ወቅታዊ ሁኔታዎችን የተመለከተ ሲሆን ፥ በተለይም በቅርቡ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ በሚገኙ አንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎች የተከሰቱትን ግጭቶች ገምግሟል።

በግምገማው ለግጭቱ መነሻ የሆኑትን ጉዳዮች በሰላማዊ መንገድ ውይይት ሊደረግባቸውና ማብራሪያ ሊሰጥባቸው ይችሉ የነበሩ መሆናቸው የተነሳ ሲሆን ፥ ነገር ግን አስቀድመው ለሁከት ተዘጋጅተው አጋጣሚዎችን ሲጠብቁ የነበሩ ፀረ-ሰላም ኃይሎች የፈጠሩት ግፊትና የነዙት የተዛባ መረጃ፤ የተደናገሩ ተማሪዎች በፈጠሩት ግጭት ፀረ-ሰላም ኃይሎች ጥፋት እንዲያደርሱ ዕድል የፈጠሩ ከመሆኑም በላይ ፥ ተማሪዎቹ የሃገራቸውን ሃብት የሚያወድምና ራሳቸውን የሚጎዳ ሁከት ውስጥ ገብተዋል ብሏል።

በዚህም በራሳቸውና በሌሎች ዜጎች ህይወትና ንብረት ላይ በደረሰው ጉዳት የተሰማውን ሃዘን ገልጿል።

በመጨረሻም በተለያዩ አካባቢዎች የተፈጠሩ ችግሮች ከህዝቡ ጋር በመነጋገር እየተፈቱ በመሆኑ ህዝቡ በተለመደው አኳኋን ሰላማዊ ኑሮውን በማከናወን ላይ ነው ያለው ኮሚቴው ፤ መንግስት የዜጎች ሰላምና መረጋጋት የማረጋገጥ ሕገ መንግስታዊ ግዴታውን ለመወጣት በእነዚህ ሕገ-ወጥ ድርጊቶች የተሳተፉ አፍራሽ ኃይሎችን ለፍትሕ የማቅረብና ከኋላ ሆነው በየአጋጣሚው ቀዳዳዎችን ለመፍጠርና ለማስፋት የሚንቀሳቀሱ የውጭ ኃይሎችን ሴራ የመመከት ስራውን አጠናክሮ እንደሚቀጠል አሰምሮበታል።