የቱሪስት መዳረሻዎች መረፊያ እና የመቆያ ስፍራ እጦት ለመፍታት ፕሮጀክቶች መንደፉን የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅት አስታወቀ

 አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 11 ፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያን የሚጎበኙ ቱሪስቶች የማረፊያ እና የመቆያ ስፍራ እጦት ለመፍታት የሚያስችል ፕሮጀክቶች መንደፉን የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅት አሰታወቀ፡፡

በኢትዮጵያ ቱሪዝም ደርጅት የመደረሻ ቦታዎች ልማትና የቱሪዝም ልማት ምርቶች ዳይሬክተር አቶ ቸርነት እንደሚሉት፥ድርጅቱ ከከተሞች ራቅ ብለው ላሉ የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎች ሊገነቡ የሚችሉ መጠለያ፣ ማረፊያ እና መዝናኛ ያካተቱ የአገልግሎት ማእከላትን በዲዛይን ደረጃ በማዘጋጀት የባለሀብቶችን መምጣተ እየጠበቀ ነው፡፡

የተዘጋጁት ዲዛይኖች በሀገሪቱ ያሉ የተለያዩ የመዳረሻ አይነቶችን ከግምት ወስጥ ያስገባ መሆኑን የገለጹት ዳይሬክተሩ፥ቀዳሚው ጎብኝዎች በፓርኮች ወስጥ የሚፈልጉትን አይነት አገልገሎት እያገኙ በምቾት ብዙ አንዲቆዩ የሚያስችል እንዲሆኑ ታስበው መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል፡፡

የተዘጋጁት ዲዛይኖች በፓርኮች ወስጥ ያለውን ሃብት መሰረት አደርገው የተሰሩ ናቸው ብለዋል፡፡

ሌላው በብዛት የአረኪዮሎጂ ጥናት የሚደረግባቸውን እንደ ሀዳር፣ መልካ ቁንጥሬ፣ የታችኛው የኦሞ ሸለቆ የመሳሰሉትን አካባቢዎች ታሳቢ ያደረገ ዲዛይን ሲሆን፤ ይህ ለምርምር የሚመጡ ተማሪዎች እና ሙሁራንን ለማስተናገድ ከላብራቶሪ እስከ መመገቢያ እና መናፈሻ ድረስ ታሳቢ የተደረገ ዲዛየን እንደሆኑ ነው ያብራሩት።

ለመንገደኛ ጎበኚዎች ምቹ አንዲሆን በየመንገዱ የሚሰሩ የማረፍያ ቦታዎችን የዚህ ዲዛይን አካል መሆኑን የተናገሩት አቶ ቸርነት ፥ከተዘጋጁት ዲዛይኖች ወስጥ አንዱን አፍሪካን ኦይል የተባለ ኩባንያ መስፈርቱን አሟልቶ ወስዷል ብለዋል፡፡

በያዝነው ወር መጨረሻ ላይም በነጭ ሳር ብሄራዊ ፓርክ አከባቢ ስራውን እንደሚጀምር ነው የጠቆሙት፡፡

አቶ ቸርነት እንደሚሉት ፥ማንኛውም ባለሃብት የተዘጋጀቱን የዲዛይን አይነቶች ተጠቅሞ ወጣ ባሉ ቦታዎች ላይ ኢንቨስት ማድረግ ቢፈልግ ፥ በዲዛይኑ መሰረት አገልግሎት መስጫ ማእከሉን የመገንባት አቅሙ ታይቶ በነፃ ከድርጅቱ ማግኘት ይችላል።

የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃና ልማት ባለሰልጣንም ፥በፓርኮች አካባቢ ለሚገነቡት አገልገሎት መሰጫዎች ቦታ በመምረጥና የእንስሳትን ደህንነት አደጋ ውስጥ የማይከቱ አሰራሮች እንዲተገበሩ በመቆጣጠር ረገድ ከቱሪዝም ድርጀት ጋር እንደሚሰራ በባለስለጣኑ የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ዳይሬክተር አቶ ግርማ ቲመር ተናግረዋል።


በትእግስት አብርሃም