ኢትዮጵያውያኑን ወደ ሃገራቸው ለመመለስ በሳዑዲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ የሰው ሃይል በመጨመር እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 11 ፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) በሳዑዲ አረቢያ የሚገኙ የመኖሪያ እና የስራ ፍቃድ የሌላቸው ዜጎችን ወደ ሀገራቸው ለመመለስ በሚደረገው ጥረት በሪያድ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ያለው መጨናነቅ እና የመረጃ ክፍተት አንድ ፈተና ሆኗል።

የሳዑዲ ዓረቢያ መንግስት በሀገሩ የመኖሪያ እና የስራ ፍቃድ የሌላቸው የውጭ ሀገራት ዜጎች ለቀው እንዲወጡ ካለፈው መጋቢት 21 እስከ መጭው ሰኔ 20 ቀን 2009 ዓ.ም ድረስ የዘጠና ቀናት የምህረት አዋጅ አውጇል።

መንግስትም አዋጁ የሚመለከታቸው በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሚመራ የአስቸኳይ ጊዜ ግብረ ሃይል አቋቁሞ እየሰራ ነው።

እስከ ዛሬ በተከናወኑ ስራዎች ወደ ሀገራቸው የተመለሱ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ግን ከሚጠበቀው አኳያ አነስተኛ ነው።

በዚህም የተነሳ መንግስት ሁሉም ባለድርሻ አካላት የከኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ጥሪ በማቅረብ ላይ ይገኛል።

በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን የወግዲ ወረዳ አመራር የሆኑት አቶ ጌታቸው ተበጀ፥ በመንግስት እየተሰጠ ያለውን መግለጫ ተከትሎ የወረዳዋ አመራሮች የተጓዥ ቤተሰቦች ልጆቻቸው ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ በሚደረገው እንቅስቃሴ ላይ ጫና እንዲፈጥሩ ቅስቀሳ እያካሄዱ መሆኑን ይናገራሉ።

ይሁን እንጅ ኢትዮጵያውያኑ በሳዑዲ ዓረቢያ ኤምባሲ ያለው መጨናነቅና የሰው ሃይል እጥረት የጉዞ ሰነድ ለመውሰድ በርካታ ቀናት እየፈጀባቸው መሆኑን ተናግረዋል።

ከትናንት በስቲያ በወላጆቿ ጉትጎታ እና ቀነ ገደቡ ቢጠናቀቅ ሊደርስ የሚችለውን አደጋ በመፍራት ወደ ሀገሯ የተመለሰችው ወጣትም፥ በሪያድ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከፍተኛ መጨናነቅ እንዳለ ተናግራለች።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታው ዶክተር አክሊሉ ገብረሚካኤል በሳዑዲ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ቁጥር በርካታ ከመሆኑ አኳያ የሰው ሃይል ቁጥር እየተጨመረ መሆኑን ጠቅሰው፥ የመረጃ ፍሰቱን የተሻለ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በሳዑዲ ዓረቢያ በሪያድ የኢትዮጵያ ኤምባሲ የዜጎች ማስመለስ አስተባባሪ ኮሚቴ የትምህርት መረጃ እና ቅስቀሳ ንዑስ ኮሚቴ አባል አቶ ኑሪ እስማኤል መሃመድ በበኩላቸው፥ የቀረበው ክፍተት መጀመሪያ አካባቢ እንደነበር አንስተው አሁን አገልግሎቱ እየተሻሻለ ነው ይላሉ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታው ዶክተር አክሊሉ ገብረሚካኤል፥ የምህረት አዋጁ ሳይጠናቅቅ ኢትዮጵያውያን እንግልት ሳይደርስባቸው ወደ ሀገራቸው እንዲገቡ የሚደረገው እንቅስቃሴ ተጠናከሮ ይቀጥላል ብለዋል።

 

 


በስላባት ማናዬ