የዘውዲቱ መታሰቢያ ሆስፒታል ተጨማሪ 18 የኩላሊት እጥበት መስጫ መሳሪያዎች ወደ አገልግሎት ሊያስገባ ነው

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 11 ፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) የዘውዲቱ መታሰቢያ ሆስፒታል ተጨማሪ 18 የኩላሊት እጥበት (ዲያሌሲስ) መስጫ መሳሪያዎች ወደ አገልግሎት ሊያስገባ ነው።

የኩላሊት እጥበት ህክምና ውድ ከመሆኑ ጋር ተዳምሮ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ማዳረስ አይቻልም።

ህክምናው አሁን ላይ በተወሰኑ የመንግስት ሆስፒታሎች እየተሰጠ ይገኛል።

ህክምናው ከሚሰጥባቸው የመንግስት ሆስፒታሎች አንዱ የሆነው ዘውዲቱ መታሰቢያ ሆስፒታል፥ ህክምናውን ተመጣጣኝ በሚባል ዋጋ ለታካሚዎች ያቀርባል።

ይህ መሆኑ ደግሞ ለህክምና የሚያወጡትን ከፍተኛ ገንዘብ እንደቀነሰላቸው ታካሚዎቹ ይናገራሉ።

የሆስፒታሉ ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር የኔአለም አየለ እንደሚናገሩት፥ ሆስፒታሉ ላለፉት ሰባት ወራት በየዕለቱ ለ20 ህሙማን ህክምናውን እየሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።

በሀገሪቱ በዚህ በሽታ የሚጠቁ ዜጎች እየበረከቱ እና የህክምናው ፈላጊዎች ቁጥርም እየጨመረ በመምጣቱ የሚሰጠው ህክምና ከህክምናው ፈላጊዎች ጋር ሊመጣጠን አልቻለም።

በዚህ ምክንያት ህክምናውን በህሙማኑ የህመም ደረጃ እና የኢኮኖሚ አቅም መሰረት ለመስጠት መገደዳቸውን ዶክተር የኔ አለም ይናገራሉ።

ሆስፒታሉ የህክምናው ፈላጊ እና የህክምናውን አለመመጣጠን ለመቀነስ አዳዲስ የኩላሊት ማጠቢያ መሳሪያዎችን ለመጨመር መወሰኑንም ነው የሚናገት።
በመጪው አመት በድምሩ 24 የኩላሊት እጥበት መስጫ መሳሪያዎች እንደሚኖሩት ይጠቅሳሉ።

መሳሪያዎቹ አገልግሎት መስጠት ሲጀምሩም የሆስፒታሉ ዕለታዊ የኩላሊት እጥበት ህክምና አቅርቦት አቅም እጅጉን ይጨምራል ብለዋል።

እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ ሰባቱ መሳሪያዎች በዚህ አመት መጨረሻ ቀሪዎቹ ደግሞ፥ በቀጣዩ አመት ወደ አገልግሎት ይገባሉ።

የህክምናው መስፋፋት እስካሁን የታየውን ህሙማኑ ከበሽታው ተላቀው ወደ ኩላሊት ንቀለ ተከላ ህክምና እንዲሸጋገሩ ያስቻለ ውጤት ይበልጥ እንዲስፋፋ ያስችላል ነው ያሉት ሜዲካል ዳይሬክተሩ።

ዳይሬክተሩ ህሙማን ህክምናውን በተመጣጣኝ ዋጋ ቢያገኙም፥ ለኩላሊት ህመም ከሚያጋልጥ የአኗኗር ዘይቤ ራስን መጠበቅ እንደሚገባቸው አንስተዋል።

 

 

በጥበበስላሴ ጀምበሩ