በኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት የፓስፖርት እደላና ስርጭት ተጀምሯል

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 11 ፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት በኩል የፓስፖርት እደላና ስርጭት ተጀምሯል።

የፓስፖርት እደላና ስርጭቱ በፖስታ ቤት በኩል መሆኑ ለዜጎች ተደራሽ ለመሆንና ምቹ አገልግሎት ለመስጠት መሆኑን የዜግነት ጉዳዮች ዋና መምሪያ ምክትል ዳይሬክተር አቶ ዘላለም መንግስቴ ተናግረዋል።

ሁለቱ ተቋማት ዛሬ በጋራ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ እንደተናገሩት፥ የፓስፖርት እደላው በሙከራ ደረጃ በአዲስ አበባ ዋናው ፖስታ ቤት ተጀምሯል።

በቀጣይም በክልል ከተሞች፣ ዞኖችና ወረዳዎች ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል ዝግጅት እየተከናወነ መሆኑንም ገልጸዋል።

የፓስፖርት ዝግጅቱ በዋና መምሪያው ከተከናወነ በኋላ ደንበኞች ፓስፖርታቸውን ከፖስታ ቤት ሄደው እንዲወስዱ፥ በሞባይል በሚላክ የጽሁፍ መልዕክት አገልግሎቱ ይሰጣል ተብሏል።

አንድ ሳምነት ያሰቆጠረው አገልግሎት የተሻለ እርካታ የታየበት መሆኑም ተገልጿል።

 

 

በትእግስት ስለሺ