ኢራን ፕሬዚዳንቷን እየመረጠች ነው

አዲሰ አበባ ፣ ግንቦት 11 ፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢራናውያን ፕሬዚዳንታቸውን ለመምረጥ ድምጽ እየሰጡ ነው።

በመላ ሃገሪቱ በተዘጋጁ ከ63 ሺህ በላይ የድምጽ መስጫ ጣቢያዎች ነው ድምጻቸውን እየሰጡ ያሉት።

የኢራን የሃገር ውስጥ ሚኒስቴር እንደገለጸው፥ በምርጫው ከ54 ሚሊየን በላይ ኢራናውያን እንደሚሳተፉ ይጠበቃል።

የሃገሪቱ የላይኛው ምክር ቤት (ጋርዲያን ካውንስል) ማመልከቻ ካስገቡት መካከል ለመጨረሻው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ስድስት እጩዎችን አቅርቦ ነበር።

ከስድስቱ እጩዎች መካከል ግን ሁለቱ ራሳቸውን ከምርጫው አግለዋል።

የቴህራን ከንቲባ ሞሃመድ ባገር ቃሊባፍ የኢብራሂም ሬይሲን ድጋፍ ከፍ ለማድረግ በሚል ራሳቸውን አግለዋል።

በአንጻሩ ምክትል ፕሬዚዳንቱ ኢሻቅ ጃንጊሪም የሃሰን ሮሃኒን የመመረጥ እድል የተሻለ ለማድረግ በሚል ከምርጫው ውጭ ሆነዋል።

በምርጫው ፕሬዚዳንት ሃሳን ሮሃኒን ጨምሮ የቀድሞው ጠቅላይ አቃቢ ህግ ኢብራሂም ሬይሲ፣ ሙስጠፋ ሃሽሚታባ እና ወግ አጥባቂው ሙስጠፋ ሚርሳሊም የመጨረሻ እጩዎች ሆነው ቀርበዋል።

ፕሬዚዳንት ሮሃኒም ምናልባት ጠንካራ ሃይማኖታዊ አስተምህሮን ያውቃሉ ከሚባሉት የቀድሞው ጠቅላይ አቃቢ ህግ እና ለአያቶላ አሊ ኻሚኒ ቅርብ ናቸው ከሚባሉት ኢብራሂም ሬይሲ ብርቱ ፉክክር ይጠብቃቸዋል ተብሏል።

የምርጫው ውጤት ዛሬ ሌሊት አልያም በነገው እለት ይፋ እንደሚሆን ይጠበቃል።

በምርጫው አንድ እጩ ከ50 በመቶ በላይ ድምጽ ማግኘት ካልቻለ፥ የመለያ ምርጫው ከሳምንት በኋላ የሚካሄድ ይሆናል።

 

 

ምንጭ፦ ቢቢሲ