ለጣና በለስ ስኳር ፋብሪካ ግንባታ ከተፈናቀሉት አርሶ አደሮች አብዛኞቹ ምትክ ቦታ አላገኙም

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 9፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአማራ ክልል በጣና በለስ ስኳር ፕሮጀክት ምክንያት የልማት ተነሺ ከሆኑ 213 አርሶ አደሮች መካከል ምትክ ቦታ ተሰጥቷቸው የግብርና ስራቸውን መቀጠል የቻሉት 11ዱ ብቻ ናቸው።

በፕሮጀክቱ ምክንያት ለተፈናቀሉ አርሶ አደሮች የአማራ ክልል ምትክ መሬት ሊሰጣቸው ስላልፈቀደ እስከ ፌዴራሉ እንባ ጠባቂ ተቋም በደረሰ አቤቱታ ተቋሙ መሬት እና ካሳው በ90 ቀናት ውስጥ ይሰጣቸው ሲል ባለፈው ጥር ወር የውሳኔ ሃሳብ አቅርቧል።

አርሶ አደሮቹ እስካለፈው መጋቢት 25 ድረስ ምትክ መሬት ማግኘት ቢኖርባቸውም እስካሁን አብዛኞቹ አልተሰጣቸውም።

የጣና በለስ ስኳር ፋብሪካ ባለቤት የሆነው የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን በፕሮጀክቱ ምክንያት ተፈናቅለው ካሳ ይገባቸዋል ለተባሉ ሁሉ ክፍያ ፈጽሚያለሁ ይላል።

ኮርፖሬሽኑ ይህንን ቢልም ከልማት ተነሺዎቹ 213 አርሶ አደሮች መካከል 36ቱ ካስ አልተከፈለንም የሚል አቤቱታ ለህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም በማቅረባቸው ተቋሙ ካሳው እንዲከፈላቸው አሳስቧል።

እነዚህ አርሶ አደሮች እስካሁን ድረስ ካሳ እንዳልተከፈላቸው ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት አረጋግጧል።

ስኳር ኮርፖሬሽን ካሳ የሚያስፈልጋቸው አርሶ አደሮችን ለይቶ የሚያቀርበው የጃዊ ወረዳ ካሳ ይገባቸዋል ብሎ ለለያቸው አርሶ አደሮች ካሳ መክፈሉን በመግለፅ የ36 አርሶ አደሮች ጉዳይ እኔን አይመለከትም ብሏል።

አጠቃላይ ሂደቱም የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ስለ ምትክ መሬትም ሆነ ስለ ካሳ ክፍያ ያቀረበው የውሳኔ ሃሳብ አልተተገበረም።

በተቋሙ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ የአስተዳደር በደል ምርመራ ዳይሬክተሩ አቶ ሀብታሙ ታደሰ፥ በተቋሙ ጥናት መሰረት ለአርሶ አደሮች ምትክ ቦታ እየተሰጠ አይደለም፤ ምትክ ቦታ ማግኘት ያለባቸው አርሶ አደሮች 213 ቢሆኑም እስካሁን ካሳ የተከፈላቸው 11 ብቻ ናቸው ይላሉ።

በክልሉ የገጠር መሬት አስተዳደር እና አጠቃቀም ቢሮ ካሳ እና ምትክ ቦታ ያልተሰጣቸውን አርሶ አደሮች በጥቃቅን እና አነስተኛ ዘርፎች በማደራጀት የስራ እድል እንዲፈጠርላቸው ለማድረግ እየተሰራ ነው ብሏል።

ከአሁን ቀደም በዜጎች አቤቱታ የተሰራውን ጥናት እና ከጥናቱ ላይ ተመስርቶ በህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም የቀረበውን ውሳኔ ያልተገበረው የአማራ ክልል መንግስት ዛሬም ለአርሶ አደሮቹ ጥያቄ ምላሽ እሰጠላሁ የሚል ቃል ገብቷል።

እንባ ጠባቂ ተቋም ደግም ውሳኔዬ ባይከበር ለክልሉ ምክር ቤት ልዩ ሪፖርት አቀርባለሁ ብሏል።

 

 

 

በዳዊት በጋሻው