ኢትዮጵያውያን ከሳዑዲ አረቢያ ወደ ሀገራቸው እንዳይመለሱ ደላሎች አፍራሽ ቅስቀሳ እያካሄዱ ነው

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 9፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ.) በሳዑዲ አረቢያ የሚገኙ የመኖሪያ እና የስራ ፍቃድ የሌላቸው ዜጎች ወደ ሀገራቸው እንዳይመለሱ ደላሎች አፍራሽ እንቅስቃሴ እና የመረጃ ክፍተት ችግር እየፈጠሩ ነው ተባለ።

ከሳዑዲ የምህረቱን አዋጅ ተጠቅመው ወደ ሀገራቸው የገቡ ኢትዮጵያዊያን፥ በተለያዩ የስራ መስኮች ሳዑዲ ውስጥ የሚሰሩ ኢትዮጵያዊያን ስለ ምህረት አዋጁ ያላቸው መረጃ አነስተኛ ነው ብለዋል።

በሳዑዲ ሪያድ የኢትዮጵያ ኤምባሲ የዜጎች ማስመለስ አስተባበሪ ኮሚቴ የትምህርት መረጃ እና ቅስቀሳ ንዑስ ኮሚቴ አባል አቶ ኑሪ እስማኤል መሃመድ በበኩላቸው፥ ዜጎችን ለማስመለስ በሚደረገው ቅስቀሳ ደላሎች እና የራሳቸውን ጥቅም የሚያስቀድሙ ዜጎች እንቅፋት እንደሆኑባቸው ተናግረዋል።

ወጣት ፍሬነሽ ያለ ስራ እና መኖሪያ ፈቃድ ለአራት አመታት በሳዑዲ አረቢያ ከኖረች በኋላ ፈቃድ አልባ ዜጎች በ90 ቀናት ውስጥ ሀገሪቱን ለቀው እንዲወጡ የተላለፈውን ትዕዛዝ ሰምታ ወደ ሀገሯ መመለሷን ገልጻለች።

ሌሎች ሶስት መሰሎቿም ትናንት ንጋት 11 ስአት ከ45 የሀገራቸውን መሬት ሲረግጡ ስሜታቸውን በከፍተኛ ደስታ ነበር የገለጹት፡፡

እነዚህ ዜጎች ወደ ሀገራቸው የተመለሱት ከምህረት ጊዜው መጠናቀቅ በኋላ ሞትን ሊያስከትል የሚችል እርምጃ እና እንግልት እንደሚመጣ በማወቃቸው ነው።

እነ ፍሬነሽ ደህንነታቸው በመረጋገጡ ያለ እንግልት እና ጉዳት ከቤተሰቦቻቸው ጋር መቀላቀላቸው ቢስደስታቸውም፥ በሳዑዲ ስለቀሩ እህት ወንድሞቻቸው ሲያስቡ ጭንቀት ይሰማቸዋል።

በሳዑዲ አረቢያ ያሉ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው የመመለስ እና አለመመለስ ጉዳይ በእነዚህ ሁለት ሃሳቦች መካከል የቆመ ነው፤ ወደ ሀገር መመለስን ደህንነት አድርግው የሚመለከቱ፥ በሌላ በኩል ወደ ቤተሰብ መመለስን ድህነት አድርገው የሚያዩም አሉ።

የዜጎቹ አስተያየት ከሁለት ምንጮች ይቀዳል። በተለይ ወደ ሀገራቸው ለመመለስ ወደ ኋላ የሚሉ ዜጎች፥ ከኋላቸው ሆነው የሚጎትቷቸው ደላላዎች መኖራቸው እየተነገረ ነው፡፡

በሳዑዲ ለመኖር የሚያስችል ፈቃድ ያላቸው ደላሎች ብዙ ኢትዮጵያውያንን ሰብስበው በመያዝ ለንግድ እያመቻቿቸው መሆኑን በሳዑዲ አረቢያ ሪያድ የኢትዮጵያ ኤምባሲ የዜጎች ማስመለስ አስተባበሪ ኮሚቴ ገልጿል።

በሳዑዲ አረቢያ ያሉ ዜጎች ሃሳብ ምንም ይሁን ምን የምህረት አዋጁ ግን አንድ ነው።

የምጣኔ ሀብት መቀዛቀዝን ተከትሎ የታወጀው አዋጅ ምህረት የለሽ ነው ተብሏል፡፡

የሳዑዲ አረቢያ መንግስት ከምህረት ጊዜው በኋላ በምድረ ሳዑዲ የሚገኙ የማንኛውም ሀገር ዜጎችን ያለ ምህርት ሀገሪቱን ለማስለቀቅ ቆርጦ ተነስቷል።

ለዚህም ከ86 በላይ እስር ቤቶችን ያዘጋጀ ሲሆን፥ በቤት ለቤት አሰሳ የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸው ዜጎችን ለማደንም ልዩ ሃይል አዘጋጅቷል።

የኢትዮጵያ መንግስት ዜጎች በምህረት ጊዜው ውስጥ ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ በተደጋጋሚ ጥሪ አያቀረበ ይገኛል።

 

 

በስላባት ማናዬ