በማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ 115 አስከሬኖችን አግኝቻለሁ - ቀይ መስቀል

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 9፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ.) በማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ ባንጋሱ ከተማ በተከታታይ ቀናት በተፈፀሙ ጥቃቶች ህይወታቸው ያለፈ 115 ሰዎችን አስከሬን ማግኘቱን የአለም አቀፉ ቀይ መስቀል ድርጅት አስታውቋል።

ከተገኙት 115 አስከሬኖች ውስጥ 34ቱ ተቀብረው የነበሩ ናቸው ብለዋል በሀገሪቱ የተራድኦ ድርጅቱ ፕሬዚዳንት አንቶኒዮ ምባኦ ቦጎ።

ከሟቾቹ ውስጥ በስለታማ ነገሮች እና በጥይት አረር የተገደሉ የሚገኙ ሲሆን፥ በመዝናኛ ስፍራዎች በብዛት የተገደሉም አሉ ብለዋል።

የሟቾቹ ቁጥር አንድ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ባለስልጣን ይፋ ካደረጉት (26) በአራት እጥፍ የበለጠ ነው።

የአልማዝ ማዕድን የሚወጣባት የባንጋሱ ከተማ ከ2013 ወዲህ ግጭት ተበራክቶባታል።

በመጋቢት 2013 የወቅቱ ፕሬዚዳንት ፍራንኮይስ ቦዚዝ በዋናነት በሴሌካ አማጺያን ከስልጣን ተነስተው በሚካኤል ጆቶዲያ ሲተኩ ሀገሪቱ ወደ ብጥብጥ መግባቷ ይታወሳል።

የመንግስታቱ ድርጅት በማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ ሰላምና መረጋጋት ለማስፈን 13 ሺህ ሰላም አስከባሪ ማስፈሩ ይታወቃል።

ይሁን እንጂ ሰላም አስከባሪ ሀይሉ ባለፈው ሳምንት በመቶዎች የሚቆጠሩ ከባድ የጦር መሳሪያዎችን የያዙ ታጣቂዎች የተቆጣጠሯትን የቦጋሱ ከተማ እስካሁን ሙሉ  በሙሉ ከታጣቂዎች ነፃ ማድረግ አልቻለም።

የመንግስታቱ ድርጅት ቃል አቀባይ ሄርቬ ቬርሆሴል፥ ሰላም አስከባሪዎቹ በአየር ላይ ጥቃት ታግዘው ዋና ዋና ቦታዎችን ከታጣቂዎቹ መንጠቅ ችለዋል ብለዋል።

 

 

ምንጭ፦ ፕሬስ ቴሌቪዥን