ነገ በሚካሄደው የፈረንሳይ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ላይ የብሄራዊ ደህንነት ጉዳይ ዋነኛ አጀንዳ ሆኗል

አዲስ አበባ ፣ ሚያዚያ 13 ፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) በፓሪስ የደረሰው የሽብር ጥቃት ነገ በሚካሄደው የፈረንሳይ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ላይ የብሄራዊ ደህንነት ጉዳይ ዋነኛ አጀንዳ እንዲሆን አድርጓል ተባለ።

ዋና ዋና እጩዎች በደህንነት ጉዳይ ላይ ያላቸው አቋም የተለያየ መሆን ደግሞ ጉዳዮ ይበልጥ ተኩረት እንዲስብ አርጎታል ነው የተባለው።

የቀኝ ዘመም ፖለቲከኛዋ ማሪን ለ ፔን በምርጫው ካሸነፉ የድንበር ላይ ቁጥጥር በማጥበቅ በሽብር ተጠርጣሪ ግለሰቦችን ከሃገር እንደሚያስወጡ ተናግረዋል።

የቀደሞው የኢኮኖሚ ሚኒስትር የነበሩትና አሁን የፕሬዚዳንታዊ ምርጫው ተፎካካሪ ኢማኑኤል ማክሮን ደግሞ፥ መፍትሄው በምርጫ ቅስቀሳዎች ላይ ቃል እንደሚገባው ቀላል አይደለም ብለዋል።

ከምርጫው በፊት በተደረገው የመራጮች ቅድመ ትንበያ መሰረትም ኢማኑኤል ማክሮን በ24 በመቶ እየመሩ ይገኛሉ።

ለ ፔን በበኩላቸው በ21 ነጥብ 5 በመቶ መራጮችን ድምፅ አግኝተዋል።

የፈረንሳይ መንግስት አሁን በስራ ላይ ካሉት 50 ሺህ በተጨማሪ ሁሉም የፀጥታ ሃይሎች በተጠንቀቅ እንዲቆሙ አድርጓል።

 

 


ምንጭ፦ ሬውተርስ