በስድስተኛው የጣና ፎረም ላይ የሚካፈሉ እንግዶች ባህር ዳር እየገቡ ነው

አዲስ አበባ ፣ ሚያዚያ 13 ፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) ከነገ ጀምሮ ለሁለት ቀናት የሚካሄደው ስድስተኛው የጣና ፎረም ጉባኤ ላይ የሚካፈሉ ከ160 በላይ እንግዶች ባህር ዳር ገብተዋል።

የማላዊና የቡሩንዲ የአሁን መሪዎች እንዲሁም የደቡብ አፍሪካ እና የቦትስዋና የቀድሞ መሪዎች እና ሌሎችም እንግዶች ባህር ዳር ከገቡት መካከል ይገኙበታል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸውም ለእንግዶቹ አቀባበል አድርገውላቸዋል።

በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጽህፈት ቤት የዲያስፖራ የህዝብ ግንኙነት እና ፕሮቶኮል ጉዳዮች ዳይሬክተር የጣና ፎረም አባል አቶ አውላቸው ማስሬ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደተናገሩት፥ እስካሁን የገቡትን ጨምሮ በአጠቃላይ 250 እንግዶች እስከ ነገ ማለዳ ባህርዳር ይገባሉ።

በክልሉ የትራንስፖርት፣ የጸጥታ፣ የመስተንግዶ እንዲሁም በሆቴል አገልግሎት ዙሪያ የተጠናከረ ዝግጅት መደረጉንም ተናግረዋል።

arrival_1.jpg

ዛሬ ከሰአት በኋላ በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ በቀድሞው የናይጀሪያ ፕሬዚዳንት ኦሊሴጎን ኦባሳንጆ አወያይነት፥ ምሁራንና ተማሪዎች የተሳተፉበትና ማህበራዊ ርዕሰ ጉዳዮችን የዳሰሰ ውይይት ተደርጓል።

በነገው እለትም ጉባኤው በተፈጥሮ ሃብት አስተዳደር ምንጭ ዙሪያ አተኩሮ እንደሚወያይ አቶ አውላቸው ገልጸዋል።

ስድስተኛው የጣና ፎረም “የተፈጥሮ ሃብት ማስተዳደር በአፍሪካ” በሚል መሪ ቃል ነው የሚካሄደው።

 

 

በታሪክ አዱኛ