የብዙሃን ማህበራትን የዴሞክራሲ ስርዓት አቅም ለማሳደግ መንግስት ድጋፍ ያደርጋል

አዲስ አበባ ፣ ሚያዚያ 13 ፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) የብዙሃን ማህበራትን የዴሞክራሲ ስርዓት አቅም ለማሳደግ መንግስት በልዩ ሁኔታ ድጋፍ እንደሚያደርግ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አባ ዱላ ገመዳ ተናገሩ።

በሃገሪቱ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ፣ የሲቪክ ማህበራት ተሞክሮ፣ ችግሮች እና ቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ በሸራተን አዲስ እየተካሄደ ይገኛል።

የምክክር መድረኩን በንግግር የከፈቱት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አባዱላ ገመዳ እንዳሉት፥ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታና መልካም አስተዳደርን ለማስፈን የሲቪክ ማህበራት፣ የህዝብ አደረጃጀቶችና የሙያ ማህበራት ጉልህ ድርሻ አላቸው።

መንግስትም የዴሞክራሲ ስርዓቱ እንዲጎለብት በየደረጃው ላሉ ምክር ቤቶች እና ብዙሃን ማህበራት ድጋፍ እያደረገ ነው ብለዋል።

ለዴሞክራሲ ስርዓቱ መጎልበትና መጠናከር የሚያደርገውን ድጋፍ በቀጣይም አጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት አፈጉባኤው።

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ከጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት እና ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም ጋር በመተባበር ባዘጋጀው የምክክር መድረክ ላይ፥ የሲቪክ ማህበራትን አለም አቀፋዊ ባህሪ እና በኢትዮጵያ እያደረጉት ያለውን ተሳትፎና አስተዋጽኦ በተመለከተ ጥናታዊ ጽሁፍ ቀርቧል።

 

የሲቪክ ማህበራቱ መንግስት የሚያከናወናቸው ስራዎች በመከታተልና ለወገኑት የህብረተሰብ ክፍል ጥቅም በማስከበር ረገድ መስራት ይኖርባቸዋል ተብሏል።

 

በምክክሩ አራት ጥናታዊ ጽህፎች የቀረቡ ሲሆን፥ የሲቪክ ማህበራት መኖርና መበራክት በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች የህብረተሱቡን ጥቅም ለማስከበር እንደሚያግዝ ተዳሷል።

 

የሲቪክ ማህበራቱ መኖር ልማት እንዲፋጠን፣ ዲሞክራሲ እንዲጎለበት፣ ተመሳሳይ ፍላጎት ያላቸው ሰዎች በማህበር ተደራጅተው ለጥቅሞቻቸው መከበር መንግስት ላይ ተጽዕኖ በማሳደር ለውጥ እንዲመጣ እንደሚያደርግ ተገልጿል።

 

ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ዶከተር አሰፋ ፍስሃ ባቀረቡት ጥናታዊ ጽሁፍ የሲቪክ ማህበራት ስልጣን ላይ ካለና ስልጣን ለመያዝ ከሚወዳደር የፖለቲካ ፓርቲ ነፃ መሆን እንደሚጠበቅባቸውአንስተዋል።

 

ሆኖም በ1997 ዓ ም ምርጫ የፖለቲካ ፓርቲዎች በቀጥታና በተዘዋዋሪ ፖለቲካ ውስጥ ሲሳተፉ ተገኝተዋል።

 

በኢትዮጵያ ሲቪክ ማህበራት ያሉምቹ ሁኔታዎችን በጥናታዊ ጽሁፋቸው ያብራሩት የኢትዮጵያ በጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ፎረም ሰብሳቢ ወይዘሮ ሳባ ገብረመድህን በበኩላቸው፥ ስለሲቪክ ማህበራት በመንግስትና በሚዲያዎች ያለው የአተያይ ችግር ሊቀረፍ ይገባል ብለዋል።

 

በጥናታዊ ጽሁፉ በኢትዮጵያ የሲቪክ ማህበራት አስተዳደራዊ ወጪን ለማስተካከል የወጣው አዋጅ ክፍተት እንዳለበትም ተገልጿል።

ከዚህ ባለፈም ማህበራቱ ከውጭ የሚያገኙት ድጎማ አነስተኛ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በአስተዳደራዊ ወጪያቸው ላይ ክፍተት ከመፍጠሩ ባለፈ፥ ማህበራቱ የአባላቶቻቸውን ጥቅም የማያስከበርላቸው በመሆኑ አዋጁ ሊሻሻል ይገባልም ነው የተባለው።

ይህም ከፅንፈኛ ፖለቲካዊ አስተሳሰብ በመውጣት ግጭትን ለመከላከልና ጠንካራ የማህበረሰብ ትስስር ለመፍጠር ተብሏል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ጸህፈት ቤት የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል የሲቪክ ማህበራት ዘርፍ ሃላፊ አቶ አብዲላዚዝ መሐመድ እንዳሉት፥ መንግስት የሲቪክ ማህበራት በልማትና ዴሞክራሲያዊ ዕድገት ላይ ሚናቸውን እንዲወጡ ይፈልጋል ለዚህም ድጋፍ ያደርጋል።

የሲቪክ ማህበራት የልማትና የዲሞክራሲ ዕድገት የሚጠናክርባቸው የተሳትፎ ሀይሎች በመሆናቸው የውስጥ አሰራሮቻቸው ላይ ሊያተኩሩ እንደሚገባም ተጠቅሷል።

ፋና ብሮድካስቲንግ በክልሎች ህዝቡ በቀጥታ የሚሳተፍባቸው መሰል የምክክር መድረኮችን በቀጣይ እንደሚያካሂድ ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ብሩክ ከበደ ገልጸዋል።

 

በበላይ ተስፋዬ