ኢትዮጵያ በቻይና በሚካሄደው ቤልት ኤንድ ሮድ ፎረም ላይ ትሳተፋለች

አዲስ አበባ ፣ ሚያዚያ 13 ፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) በመጪው ግንቦት ወር በቻይና በሚካሄደው የቤልት ኤንድ ሮድ ፎረም አለም አቀፍ የትብብር ጉባኤ ላይ ኢትዮጵያና ኬኒያን ጨምሮ ለ28 ሃገራት የተሳትፎ ማረጋገጫ መስጠታቸውን የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ድረ ገጽ አስነብቧል።

በጉባኤው ላይ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ፣ የአለም ባንክ ፕሬዚዳንት ጂም ዮንግ ኪም እና የአለም አቀፉ የገንዘብ ፈንድ ዳይሬክተር ክርስቲያን ላጋርድ ይታደማሉ።

በአጠቃላይ 1 ሺህ 200 ምሁራን፣ የመንግስት ባለስልጣናትና የመገናኛ ብዙሃን ተወካዮች እንዲሁም ከ110 ሃገራት እና ከ61 አለም አቀፍ ተቋማት የተውጣጡ ተሳታፊዎች ይገኛሉ ተብሏል፡፡

የሃገሪቱ የእድገትና የሪፎርም ኮሚሽን ምክትል ዳይሬክተር ዋንግ ዢአኦታ፥ ግንቦት 6 እና 7 ቀን 2009 የሚደረገው ጉባኤ የቻይናው ፕሬዚዳንት ዢ ሺን ፒንግ የቻይናን ሲልክ ኤንድ ሮድ ፕሮጀክት ይፋ ካደረጉ በኋላ የሚከናወን ታላቅ ጉባኤ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

ዋንግ ዢአኦታ ፈተናዎችን ለመጋፈጥ ሐሳቦችንና እውቀቶችን በመሰብሰብ አዲስ መደላድል መፍጠር እንደሚገባ ጠቅሰው፥ የተለየ የእድገት ንድፍ በማስቀመጥ የጋራ የልማት መንገድ መፈለግ አለብንም ብለዋል።

በጉባኤው ላይ የመሪዎች የክብ ጠረጴዛ ውይይት የሚከናወን ሲሆን፥ በከፍተኛ ኃላፊዎች መካከልም ምክከር ይደረጋል ሲል ድረ ገፁ አስነብቧል፡፡

በዚህም ቻይና ከ20 ሃገራት ጋር የትብብር ስምምነት ትፈራረማለች ተብሎ ይጠበቃል።

የጉባኤው የትኩረት አቅጣጫ በመሰረተ ልማት፣ በኢንዱስትሪ ኢንቨስትመንት፣ በኢኮኖሚና ንግድ ትብብር፣ በሐይልና በተፈጥሮ ሃብት፣ በገንዘብና በባህል ልውውጥ ላይ ይሆናል ተብሏል፡፡

 

 


ምንጭ፦ ኢዜአ