የመንግስታቱ ድርጅት ሰሜን ኮሪያ የሚሳኤል ሙከራዋን እንድታቆም አስጠነቀቀ

አዲስ አበባ ፣ ሚያዚያ 13 ፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) ሰሜን ኮሪያ በተደጋጋሚ የምታደርገውን የሚሳኤል ሙከራ እንድታቆም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት አስጠነቀቀ።

ምክር ቤቱ ፒዮንግያንግ እያደረገች ያለውን የሚሳኤል ሙከራ ኮንኖታል።

ምናልባት ከዚህ ድርጊቷ የማጥቆጠብ ከሆነም ተጨማሪ ማዕቀብን ለመጣል እገደዳለሁ ብሏል።

ሃገሪቱ እያደረገች ያለው እንቅስቃሴ በአካባቢው ብሎም በሃገራት መካከል ውጥረትን የሚያነግስ መሆኑንም ገልጿል።

የፀጥታው ምክር ቤት ሰሜን ኮሪያ በዚህ ድርጊቷ ከገፋች ስድስት ተጨማሪ ማዕቀቦችን ለመጣል ማቀዱም ታውቋል።

በመንግስታቱ ድርጅት የአሜሪካ አምባሳደር ኒኪ ሃሌይ በበኩላቸው፥ ፒዮንግያንግ ስጋት ናት ብለዋል።

ሩሲያ በበኩሏ 15 የጸጥታው ምክር ቤት አባል ሃገራት ያሳለፉትን ስምምነት ውድቅ አድርጋዋለች።

በአንጻሩ የፒዮንግያንግ አጋር የምትባለው ቻይና ለስምምነቱ ድጋፏን አሳይታለች።

የፀጥታው ምክር ቤት የወቅቱ ሊቀመንበር የሆነችው አሜሪካ፦ በውጪ ጉዳይ ሚኒስትሯ ሬክስ ቲለርስን መሪነት በመጭው ሳምንት ከሰሜን ኮሪያ ባለስልጣናት ጋር በጉዳዩ ዙሪያ ለመነጋገር አቅዳለች።

ሰሜን ኮሪያ በተደጋጋሚ የኒውክሌር ጦር መሳሪያ መሞከሯ በበርካቶች ዘንድ ውግዘትን እያስከተለባት ነው።


ምንጭ፦ ዘ ጋርዲያን