አህመዲን ነጃድ ከኢራን ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የመጨረሻ እጩዎች ውጭ ሆኑ

አዲስ አበባ ፣ ሚያዚያ 13 ፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) የቀድሞው የኢራን ፕሬዚዳንት ሞሃመድ አህመዲን ነጃድ በመጭው ወር ከሚካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ውጭ መሆናቸው ተሰማ።

ነጃድ 12 አባላት ባሉትና እንደ ህግ አውጭ በሚያገለግለው የሃገሪቱ የላይኛው ምክር ቤት፥ በቀጣዩ ወር ከሚካሄደው የሃገሪቱ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የመጨረሻ እጩዎች ውጭ ተደርገዋል።

በቀጣዩ ወር መጀመሪያ ላይ ለሚካሄደው የኢራን ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ከ1 ሺህ 6 መቶ በላይ እጩዎች ለላይኛው የሃገሪቱ ምክር ቤት (ጋርዲያን ካውንስል) ማመልከቻቸውን አስገብተው ነበር።

በሃገሪቱ መንፈሳዊ መሪ አያቶላ አሊ ኻሚኒ በተሾሙ አባላት የሚመራው ምክር ቤትም የመጨረሻ እጩ ተወዳዳሪዎችን ይፋ ሲያደርግ፥ የቀድሞውን የሃገሪቱን ፕሬዚዳንት ከዝርዝሩ ውጭ አድርጓቸዋል።

ተቀማጩ ፕሬዚዳንት ሃሰን ሮሃኒ፣ ኢብራሂም ሬይሲ፣ የቴህራን ከንቲባ ሞሃመድ ባገር ጋሊባፍ፣ የቀድሞው ምክትል ፕሬዚዳንት ኢሻቅ ጃንጊሪ፣ ሞስጠፋ ሚርሳሊም እና ሞስጠፋ ሃሽሚታባም የመጨረሻዎቹ እጩዎች ሆነው ግንቦት ወርን ይጠባበቃሉ።

ሃሰን ሮሃኒም ከኢብራሂም ሬይሲ እና የቴህራን ከንቲባ ከሆኑት ሞሃመድ ባገር ከባድ ፉክክር ይጠብቃቸዋል ተብሏል።

በተለይም የእስላማዊ ህጎች ፕሮፌሰሩ ሬይሲ ለሮሃኒ ብርቱ ባለጋራ ይሆናሉም ነው የተባለው።

የ56 አመቱ ሬይሲ በፕሬዚዳንትነት ከተመረጡ በሃገሪቱ ያለውን ሙስና እና ድህነት ለመቀነስ እንደሚሰሩ ቃል ገብተዋል።

የሃገሪቱን ጠንካራ ሃይማኖታዊ አስተምህሮ ያውቃሉ የሚባሉት ሬይሲ፥ ሃገራቸውን በጠቅላይ አቃቢ ህግነትም አገለግለዋል።

ግለሰቡ የሃገሪቱን መንፈሳዊ መሪ አሊ ኻሚኒን የመተካት እድል እንዳላቸውም ይነገራል።

ኢራንን ከ2005 እስከ 2013 በፕሬዚዳንትነት ያገለገሉት ሞሃመድ አህመዲን ነጃድ፥ በፕሬዚዳንትነት እንደሚወዳደሩ ሲያሳውቁ በበርካቶች ዘንድ ግርምትን ፈጥሮ ነበር።

አያቶላህ አሊ ኻሚኒም የቀድሞው ፕሬዚዳንት በምርጫው እንዳይሳተፉ ፍላጎት ነበራቸው ተብሏል።

የላይኛው ምክር ቤት (ጋርዲያን ካውንስሉ) የኢራን ፓርላማ ወይም መጅሊሱ የሚያሳልፋቸውን ውሳኔዎች የማጽደቅ እና የመሻር ሙሉ ስልጣን ያለው አካል ነው።

ምክር ቤቱ የሃገሪቱን ፕሬዚዳንታዊ እጩዎች የሚለይ ሲሆን፥ ምንም አይነት ሴት እጩዎችን አያካትትም።

 

 

 


ምንጭ፦ አሶሺየትድ ፕረስ