ቻይና የመጀመሪያዋን ቲያንዡ-1 እቃ ጫኝ መንኮራኩር ወደ ጠፈር ላከች

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 12፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ቻይና የመጀመሪያዋን ቲያንዡ-1 የተሰኘች እቃ ጫኝ መንኮራኩር ወደ ጠፈር ዛሬ አምጥቃለች፡፡

በዚህም ቻይና በህዋ ሳይንስ እና በጠፈር ኢንዱስትሪው ስኬት እያስመዘገበች ለመሆኑ ማሳያ ነው ተብሎላታል፡፡

ቲያንዡ-1 የተላከችው በደቡብ ሃይናን ግዛት ከሚገኘው ዌንቻንግ ከተባለው የሀገሪቱ የጠፈር ምርምር ማዕከል ነው፡፡

መንኮራኩሯ 10 ነጥብ 6 ሜትር ርዝመት እና 3 ነጥብ 35 ሜትር የዙሪያ ስፋት አላት፡፡

ክብደቷም 13 ነጥብ 5 ቶን ሲሆን 6 ነጥብ 5 ቶን ክብደት ያላቸውን እቃዎች መሸከም ትችላለች፡፡

የቻይና የህዋ ሳይንስ ተመራማሪዎች ቲያንዡ-1 ግዘፏ የእቃ ጫኝ መንኮራኩር መሆኗን ገልጸዋል፡፡

መንኮራኩሯ በጠፈር ምህዋር ላይ ለምትገኘው ለቲያንጎንግ-2 መንኮራኩር ቤተ ሙከራ ነዳጅ ፣ ምግብ፣ ውሃ እና ሌሎችንም የምርምር ቁሶችን እንደምታደርስ ይጠበቃል፡፡

የጫነችውን እቃ በምህዋሩ ላይ ለማራገፍም በርካታ ሂደቶችን እንደሚያልፍ የተገለጸ ሲሆን በርካታ ቀናትንም የወስዳል ተብሏል፡፡

ቲንጎንግ-2 የምርምር መንኮራኩር 10 ነጥብ 4 ሜትር ርዝመት 3 ነጥብ 35 የዙሪያ ስፋት እና 8 ነጥብ 6 ቶን ክብደት አላት፡፡

ቲያንዡ-1 እቃ ጫኝ መንኮራኩር ለሙከራ ያህል ሶስት ጊዜ ወደ ቲያንጎንግ-2 መንኮራኩር እቃ እንድትውስድ እንደሚደረግ ተጠቁሟል፡፡

ቤጂንግ በ2022 ቋሚ የህዋ ላይ የምርምር ጣቢያ እንዲኖራት አቅዳ እየሰራች ነው፡፡

የህዋ ዓለም ለሰላማዊ ዓላማዎች እንደምትጠቀምበት ገልጻለች ቻይና፡፡

ምንጭ፡- ፕሬስ ቲቪ