ሃሰተኛ የፍርድ ቤት ማህተም በመጠቀም የሚፈጸሙ ወንጀሎች ቁጥራቸው እየጨመረ ነው

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 12፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ሃሰተኛ የፍርድ ቤት ማህተም በመጠቀም የሚፈጸሙ ወንጀሎች ቁጥራቸው እየጨመረ መምጣቱ ተገለፀ፡፡

ይህ ወንጀል ግለሰቦች ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት የሚፈጽሙት ቢሆንም፥ ህዝቡ በፍርድ ቤቶች ላይ እምነት እንዳይኖረው በማድረግ የሚፈጥረው አሉታዊ ተጽእኖ ከፍተኛ መሆኑን የፌደራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ይገልጻል።

ማህተሙ የፍርድ ቤት መሆኑን የተረዱ አታላዮች የራሳቸውን ውሳኔ ጽፈው፥ የተከበረውን የፍርድ ቤት ማህተም ቀርጸው የሚፈልጉትን ለማስፈጸም ወንጀል ይሰራሉ።

የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄኔራል ጽህፈት ቤት ሃላፊው ረዳት ኮሚሽነር የማነ ገሰሰ፥ የኮሚሽኑ ምርመራ ክፍል በቅርቡ የባህር ትራንዚትና ትራንስፖርትን 46 ሚሊየን ብር ህገወጥ ሰነድ እና ማህተም ተጠቅመው ከባንክ ሊያወጡ የሞከሩ ግለሰቦችን እጅ ከፍንጅ መያዙን ነው የገለጹት፡፡

የአንድ አቅመ ደካማ መኖሪያ ቤትን እስከ መቀማት የደረሰ ወንጀል በዚሁ በሃሰት በተዘጋጀ የፍርድ ቤት ማህተም እስከመጸምም ተደርሷል።

የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ማህተሙ በህገወጥ መንገድ ተመሳስሎ ተሰርቶ የፍርድ ቤቱ ውሳኔ በማስመሰል ወንጀሎች ሲፈጸሙ መደረሱን፥ የፍርድ ቤቱ ምክትል ፕሬዝዳንት በሪሁ ተወልደ ብርሃን ተናግረዋል።

አቶ በሪሁ ማህተሙን ተጠቅሞ የሚፈጸመው ወንጀል አንድም ትክክለኛውን በመስረቅ፥ ሲቀጥልም አመሳስሎ በመስራት መሆኑን አስረድተዋል።

በዋናነት የቤተሰብ፣ የጉዲፈቻ እና የውርስ ጉዳዮች የፍርድ ቤቱን ማህተም በማስመሰል በተቀረጹ ማህተሞች ውሳኔ እየተሰጣቸው ተገኝተዋል ነው ያሉት፡፡

በዚህ መልኩ በተፈጸመ ወንጀል ባለፈው ዓመት ከ10 በላይ ተከሳሾች እስከ ሰባት ዓመት በሚደርስ እስራት ተቀጥተዋል።

ይህ ወንጀል ወደ ዘንድሮው ዓመት ሲሻገር በወንጀሉም በወንጀሉ ፈጻሚዎችም የጨመረ ሲሆን፥ እስካሁን ድረስ 36 የፍርድ ቤት ማህተም እያዘጋጁ ጥቅም ላይ ሲያውሉ በቁጥጥር ስር የዋሉ ግለሰቦች ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ ይገኛል።

ከእነዚህ ውሰጥ 15ቱ በመጋቢት ወር የተያዙ መሆናቸው፥ ችግሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ ከፍ እያለ መምጣቱን ያሳያል።

ሁኔታው ለግል ጥቅም ማግኛ ተብሎ የሚፈጸም ቢሆንም የፍትህ ስርዓቱ ላይ መዛባትን በማስከተል፥ ህዝቡ በፍትህ ተቋማት ላይ አምነት እንዲያጣ የማድረግ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳላቸው፥ የፌዴራል ዋና ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ አቶ ጌታቸው አምባዬ ይናገራሉ።

ከዚህ መነሻም በወንጀሉ ጉዳይ የመጀመሪያው ተጎጂ ህብረተሰቡ በመሆኑ የክስ ሂደቱ ይበልጥ እንዲጠብቅ ይደረጋል ነው ያሉት።

አቶ በሪሁ በበኩላቸው ለአፈጻጸምና ለተለያዩ ፋይናንስ ተቋማት የሚቀርቡ የፍርድ ቤት ሰነዶች፣ የፍርድ ቤት ማህተም ስላረፈባቸው ብቻ ከመቀበል ይልቅ ውሳኔዎቹን በተመለከተ ማረጋገጫ መጠየቅ ይገባል ብለዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የክትትል ስርዓት በመዘርጋት ለግለሰቦችም ሆነ ለተቋማት ማረጋገጫ በማዘጋጀት ወንጀሉን የመከላከል ስራ ይሰራል ነው ያሉት።

 

 

 

 

 

 

በታሪክ አዱኛ