በኦሮሚያ ክልል ከሚገኙ 10 ሺህ ባለሃብቶች መካከል ወደ ስራ የገቡት 46 በመቶዎቹ ብቻ ናቸው

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 12፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) አብዛኞቹ ባለሃብቶች ለልማት የወሰዱትን መሬት ከሰባት እስከ ስምንት ዓመታት አጥረው ያስቀመጡ በመሆኑ፥ ክልሉ እርምጃ መውሰድ መጀመሩን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳ ተናግረዋል።

የኦሮሚያ ከልል ለኢንቨስትመንት አመቺ የሆነ መልክዓ ምድር፣ የተፈጥሮ ሃብትና ሰፊ የሰራተኛ አቅም ያለው ቢሆንም፥ የዘርፉ አሰራር ችግሮች እና ልማታዊ ያልሆኑ ባለሀብቶች መስፋፋት ትልቅ ተግዳሮት እንደሆነ ይነገራል።

ይህንኑ ችግር ለመፍታት የክልሉ መንግስት የተለያዩ የማሻሻያ ስራዎች እየሰራ ሲሆን፥ በዛሬው እለትም በክልሉ የሚገኙ ባለሀብቶችን ያሳተፈ ምክክር አካሂዷል፡፡

ባለሃብቶቹ በአሁኑ ወቅት በክልሉ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ላይ የመሰረተ ልማት አለመሟላትን ጨምሮ የሚስተዋሉትን ክፍተቶች አንስተዋል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳ፥ የመሰረተ ልማት ችግርን በተመለከተ ክልሉ ባለው አቅም ለማዳረስ እየሰራ ነው ብለዋል።

የህዝብ ፍላጎት መጨመር እና የክልሉ የአቅም ውስንነት ለችግሮች መፈጠር በምክንያትነት ጠቅሰው፥ ልማታዊ ባለሀብቱ አልተበረታታም የሚለውን ሀሳብ በቀጣይ ትክክለኛ ሁኔታ ሊታይ እንደሚገባው ነው አቶ ለማ የተናገሩት፡፡

የክልሉ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን እና መሬት አስተዳደር ተቋማት በተናጠል መስራታቸው ለችግሩ አስተዋጽኦ አለው በሚል ከባለሃብቶቹ ለቀረበው ጥያቄም፥ ክልሉ የተሻለ ያለውን ማስቀመጡን ርዕሰ መስተዳድሩ ገልፀዋል፡፡

ወደፊት ችግር የሚፈጠር ከሆነ ጥናት ላይ የተመሰረተ እርምት እንደሚወሰድም ነው ያስረዱት።

የዘርፉ ትልቁ ማነቆ የሀገሪቱ ትልቅ ሀብት የሆነውን መሬት ወስዶ ያለስራ የሚያስቀምጥ ጸረ ልማት ባለሀብት መሆኑን የገለጹት አቶ ለማ፥ ከዚህም ባለፈ ህጋዊ ፍቃድ ይዘው ስራ የጀመሩ ባለሀብቶችም ባላቸው አምስት ሄክታር ላይ ከሶስት እስከ አራት ሄክታር መሬት ጨምሮ ማጠር በስፋት የሚታይ ችግር መሆኑን አንስተዋል፡፡

በገጠር አካባቢ ያለው የዘርፉ ማነቆ ከዚህም የከፋ መሆኑን ይናገራሉ፡፡

እነዚህን ችግሮች ለመፍታት እየተወሰዱ ያሉ ችግሮችን፥ ክልሉ ለኢንቨስትመንት ጥሩ አመለካከት እንደሌለው አድርጎ መመልከት ተገቢ አለመሆኑንም ነው ርዕሰ መስተዳድሩ የተናገሩት፡፡

የተሻለ ኢንቨስትመንትን ለመሳብና የሚሰሩ ባለሃብቶች እንዲሰማሩ ለማድረግ ያለመ እርምጃ እየተወሰደሰ መሆኑንም አብራርተዋል።

ክልሉ በአቋራጭ ያልተገባ መሬት ለማግኘት የሚሞክሩ ባለሀብቶችን እና ደላላዎችን የማጥራት ስራ እየተሰራ ባለበት ሂደት ባለሀብቶችም ከድርጊቱ እንዲቆጥቡ አሳስበዋል፡፡

ከዚህም ባለፈ የክልሉ መንግስት ባለሃብቶችን እያባረረ ነው በሚል የሚናፈሰው ተራ አሉባልታ መሆኑን ባለሀብቱ ተረድቶ ያለ ስጋት ተግባሩን እንዲያከናውን ጠይቀዋል፡፡

የዘርፉን ማነቆ ለማጥራት እና የኢንቨስትመንት ልማትን ለማስፋፋት የሚያስችል ዘመናዊ አሰራርም እየተዘረጋ ሲሆን ባለሃብቱም የራሱን አስተዋፅኦ እንዲያደርግ በውይይቱ ወቅት ጥሪ ቀርቧል።

 

 

 

 

 

 

 

በሰርካለም ጌታቸው