ኢትዮጵያ የድርቅ አደጋን በራሷ አቅም እየተቋቋመች መሆኗ ትልቅ ስኬት ነው- ኮሚሽነር ምትኩ ካሳ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 12፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ሀገሪቱ በዋናነት በራስ አቅም የድርቅ አደጋን እየተቋቋመች መሆኗ ትልቅ ስኬት እንደሆነ ብሔራዊ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽነሩ ምትኩ ካሳ ተናገሩ፡፡

በድርቁ የተጎዱ ወገኖችን ለመታደግም መንግስት የአንበሳውን ድርሻ በመያዝ በየወሩ ምግብና ምግብ ነክ እርዳታ ሳይቆራረጥ እየሰጠ እንደሆነ አቶ ምትኩ ገልፀዋል፡፡

ሆኖም ከችግሩ ስፋት አንፃር በራስ አቅም መንግስት ከሚሰራው የእርዳታ ስራ ጎን ለጎን የውጭ የረድኤት ተቋማትና የአለም አገራት የሚያደርጉት ድጋፍ አናሳ በመሆኑ ድጋፋቸውን ሊያጠናክሩ እንደሚገባ ነው የገለጹት፡፡

ኮሚሽነሩ በያዝነው ዓመት ጥር ወር ላይ መንግስት የድርቅ አደጋውን ለመታደግ 948 ሚሊዮን ዶላር የውጭ እርዳታ ያስፈልጋል ቢልም 93 ሚሊዮን ዶላር ብቻ መገኘቱን በማሳያነት አንስተዋል፡፡

ዓለም አቀፍ የአየር መዛባት ክስተትን ተከትሎ በሀገሪቱ በተፈጠረው የድርቅ አደጋ የአንድም ሰው ህይወት ሳያልፍ እርዳታ እየተሰጠ መሆኑ ትልቅ ስኬት ነው ብለዋል፡፡

አሁን ላይ ድርቁ የተከሰተው በደቡብና በደቡብ ምስራቅ የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ ሲሆን፥ በቀጣይ ድርቁን ለመቋቋም ዘላቂ የልማት ማዕቀፍ ስራዎችን ማዕከል ተደርጎ መሰራት እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡

የአካባቢ ጥበቃ፣ የመስኖ ልማት፣ የውሃ ማቀብ እና የደን ልማት ስራዎች እንዲሁም የሀገሪቱን ኢኮኖሚ እድገት አጠናክሮ የማስቀጠል ስራዎች በተጠናከረ ሁኔታ እንደሚተገበሩ ነው ያመላከቱት ኮሚሽነሩ፡፡

ካለፈው ዓመት ጀምሮ በተከሰተው የድርቅ አደጋ ተጎጂ ወገኖችን ለመታደግ መንግስት 100 ሚሊን ዶላር ገደማ ወጪ ማድረጉን ከብሔራዊ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የተገኙ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

ምንጭ፡-ኢብኮ