ምክር ቤቱ በአንዳንድ አካባቢዎች ተከስቶ የነበረውን ሁከት አስመልክቶ የቀረበውን ሪፖርት አጸደቀ

አዲስ አበባ ፣ ሚያዚያ 12 ፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በኦሮሚያ እና አማራ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች እንዲሁም በደቡብ ክልል ጌዲኦ ዞን የተከሰተውን ግጭት አስመልክቶ ያቀረበውን ሪፖርት አጸደቀ።

ምክር ቤቱ በየደረጃው ባሉ የመንግስት አካላትና ተመጣጣኝ ያልሆነ እርምጃ በወሰዱ የፀጥታ ሃይሎች ላይ ማጣራት ተደርጎ ለህግ እንዲቀርቡ በኮሚሽኑ የተሰጠውን ምክረ ሃሳብም ደግፏል፡፡

በብሄር ተኮር ጥቃት ከአካባቢያቸዉ የተፈናቀሉ ዜጎችም በአፋጣኝ ይቋቋሙ ብሏል ምክር ቤቱ።

ከዚህ ባለፈም በጌዲኦ ዞን ብሄርን መሰረት ባደረገ ጥቃት ላይ ተሳትፎ ያደረጉ የመንግስት የስራ ሀላፊዎች፣ የጸጥታ አካላት እና የጌዲኦ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት እንዲጠየቁም ወስኗል።

በተመሳሳይ በባህርዳር በነበረዉ ሁከት ተሳትፎ ያደረገው የሰማያዊ ፓርቲ እና በኦሮሚያ ለተፈጠረው ቀውሰ የአባባሽ ሚና የተጫወተው የአሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፊኮ) አባላት ይጠየቁ ሲልም ውሳኔ አሳልፏል።

 

 


በብስራት መለሰ