የድሬዳዋ አስተዳደር በ167 የመንግስት ሰራተኞች እና 110 አመራሮች ላይ እርምጃ ወሰደ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 12፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በድሬዳዋ አስተዳደር ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ባልተወጡና ለመልካም አስተዳደር ችግሮች ምክንያት ናቸው በተባሉ 167 የመንግስት ሠራተኞችና 110 አመራሮች ላይ እርምጃ መወሰዱን ከንቲባ ኢብራሂም ዑስማን ተናገሩ።

እርምጃው የተወሰደው ባለፉት ሦስት ወራት ከከፍተኛ አመራር እስከ ሠራተኛው ድረስ በተካሄደው፥ ጥልቅ የተሃድሶ ግምገማ ላይ የተለዩ ችግሮችን መሰረት በማድረግ ነው ብለዋል ከንቲባው ፡፡

እንደ መንግስት፣ እንደ ድርጅት እንዲሁም በየደረጃው ከሚገኘው የሕብረተሰብ ክፍሎች ጋር በተካሄደው ጥልቅ የተሃድሶ ውይይት መድረክ ላይ አመራሩ በተሰጠው ሥልጣን ሕዝብን ከማገልገል ይልቅ ራሱን ሲጠቅም መቆየቱ ተመልክቷል፡፡

በእዚህ በኩል አስተዋጽኦ በነበራቸው 110 አመራሮች ላይ እርምጃ መወሰዱን ጠቅሰው፥ ከነዚህም ውስጥ 13 አመራሮች ከስልጣናቸው እንዲነሱ መደረጉን አስታውቀዋል፡፡

ሕዝብን ለምሬትና ለመልካም አስተዳደር ችግሮች ሲዳርጉ የነበሩና በሙስና ተግባራት የተሰማሩ 42 ሠራተኞች ከሥራ እንዲሰናበቱ ሲደረግ፥ በ75 ሠራተኞች ላይ ከቀላል እስከ ከባድ የዲሲፒሊን ቅጣት እርምጃ ተወስዷል።

በተጨማሪም 29 የመንግስት ሠራተኞች ወደ ሌላ ቦታ እንዲሸጋሸጉ ተደርጓል።

በ21 ሠራተኞች ላይ መረጃ የማጥራት ሥራ እየተሰራ መሆኑንና በዘጠኙ ቀበሌዎች የተመደቡ ደንብ አስከባሪዎች፥ በፈጠሩት ከፍተኛ ችግር ሁሉም ውላቸው ተቋርጦ እንዲሰናበቱ መደረጉን አስረድተዋል።

ምንጭ፡-ኢዜአ