አዲስ የግብርና ኤክስቴንሽን ሰትራቴጂ ተዘጋጀ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 11፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በጥናት የገበያ ፍላጎት ላይ የተመሰረተ የአመራረት ሰርዓትን የሚከተልና እሴት የሚጨምር የግብርና ኤክስቴንሽን ሰትራቴጂ ተዘጋጀ።

የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ ጋር በትብብር ጥናት አካሂዶ ነው ስትራቴጂውን ይፋ ያደረገው።

የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስትር ዶክተር እያሱ አብርሀ እንዳሉት፥ የግብርና ኤክስቴንሽን ባለፉት አመታት የግብርናው ዘርፍ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ድህነትን ለማስወገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል።

አሁን ካለው ፍላጎትና የሀገሪቱ ቀጣይ የልማት አቅጣጫ አንጻር ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ላይ የተመሰረተውን የግብርና ኤክስቴንሽን ስትራቴጂ ወደ ገበያ ተኮርና እሴት መጨመር ላይ ለማተኮር ነው አዲሱ ስትራቴጂ የተዘጋጀው።

የጋራ የግብይት ስርአት በመፍጠር በክላስተር ሰብሎችን በብዛትና በተመሳይ ጥራት ማምረት በስትራቴጂው ተቀምጧል።

የኤክስቴንሽን ባለሙያዎች ገበያ ተኮር መረጃን ለአርሶ አደሩ እንዲያቀርቡም ይደረጋል።

መረጃዎቹ የሴቶችና ወጣቶችን ፍላጎት በመለየት ችግሮቻቸውን በሚፈቱ መልኩ ይሰናዳሉም ነው የተባለው።

ይህም አርሶ አደሮችን ይበልጥ ተጠቃሚ የሚያደርግና የአግሮ ኢንዱሰትሪ ፓርኮችን የሚመግብ የግብርና ምርት እንዲሆን ያስችላል።

የግብርናውን ዘርፍ እንደሚያዘምነው የሚጠበቀውን የኤክስቴንሽን ሰትራቴጂ ክልሎች እንደየነባራዊ ሁኔታቸው ተግባር ላይ እንደሚያውሉት ተገልጿል።


በበላይ ተስፋዬ