ኤጀንሲው በተቋማት አለመናበብ የተነሳ የሚደርሰውን የአገልግሎት መቆራረጥ ለማስቀረት እየሰራ ነው

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 11 ፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የፌዴራል የተቀናጀ የመሰረተ ልማቶች ማስተባበሪያ ኤጀንሲ በመሰረተ ልማት አቅራቢ ተቋማት አለመናበብ ምክንያት ይደረስ የነበረውን የሀብት ብክነት እና አገልግሎት መቆራረጥ ለማስቀረት የሚያስችሉ ተግባራትን ማካሄድ ጀምሯል።

በበጀት ዓመቱ መጀመሪያ ላይ የተቋቋመው ኤጀንሲው፥ የመንገድ፣ የባቡር፣ የአውሮፕላን ማረፊያ፣ የስልክ፣ የውሃና የኤሌክትሪክ መስመር ፕሮጀክቶችን ነው የሚያቀናጀው።

በኤጀንሲው የፕሮግራም ትውውቅና የማስተር ፕላን ዳይሬክተር አቶ ሮቤል በቀለ፥ እነዚህ ተቋማት ተቀናጅተው መስራታቸው ቀደም ሲል በሀገር ሃብት ላይ ይደርስ የነበረውን ብክነት የሚያስቀር ነው ብለዋል።

እንዲሁም በአካባቢና በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ይደርስ የነበረውን ጉዳት የሚያስወግድ መሆኑን ገልፀዋል።

የመሰረተ ልማት አቅራቢ ተቋም ከሆኑት አንዱ የሆነው የኢትዮ ቴሌኮም የኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ሃላፊ አቶ አብዱራሂም አህመድ፥ ቀደም ሲል ያለቅንጅት እና ያለ ጋራ እቅድ ሲሰራ በርካታ ጉዳቶች ያጋጥሙ እንደነበር ተናግረዋል።

ማንኛውም አገልግሎት የሚዘረጋው መንገድን ተከትሎ በመሆኑ የአንዱ መፍረስ ወይም መገንባት የሌላውን ስራ የሚነካ በመሆኑ ለተቋሙ የአገልግሎት መቆራረጥ መንስኤ ይሆን እንደነበር አንስተዋል።

አሁን ላይ ግን በቅንጅት መሰራቱ ተቋማቱ የተሻለ አፈጻጸም እንዲኖራቸውና የሀገር ሃብትም ከብክነት እንዲድን ያደርጋል ነው ያሉት አቶ አብዱራሂም።

ኤጀንሲውም የተጠቀሱትን ፋይዳዎች ለማምጣት የሚያስችሉ ሃላፊነቶችን የያዘ ሲሆን፥ የተቋማቱን እቅድ ከመፈተሽና ከማቀናጀት ባሻገር የማስተባበርና ፍቃድ የመስጠት ሃላፊነት አለበት። ተቋማቱ የሚያቀርቧቸው እቅዶች የተቋሙን ይሁንታ ሳያገኙ ወደ ስራ መግባት አይችሉም።

በኤጀንሲው የመሰረተ ልማት ስራዎች ፍቃድና ክትትል ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ገብረመድህን፥ የግንባታ ፍቃድ ለማግኘት ከሌሎቹ ተቋማት ጋር መቀናጀት ብቻ ሳይሆን ሌሎች ጉዳዮችም ከግምት ውስጥ እንደሚገቡ ተናግረዋል።

ኤጀንሲው በአሁኑ ወቅት አዲስ በሚሰሩ መሰረተ ልማቶች ላይ ሃላፊነቱን ለመወጣት የሚያስችል ዝግጅት ያጠናቀቀ መሆኑንም ነው አቶ ሰለሞን ያስታወቁት።

ቀደም ሲል በግንባታ ውስጥ በገቡ ፕሮጀክቶች ላይ በቅንጅት አለመፈጠር ምክንያት ያጋጠሙ ችግሮችን ለመፍታት የማስተባበር ሚናውን እየተወጣ መሆኑንም ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

ኤጀንሲው የመሰረተ ልማት ተቋማቱን ከማቀናጀት ጎን ለጎንም በሚገነቡ ፕሮጀክቶች ምክንያት ከይዞታቸው ለሚነሱ ዜጎች የካሳ ቀመር የሚያዘጋጅ ሲሆን፥ የካሳውን አፈጻጸምም ይከታተላል።

በትእግስት ስለሺ