የከተማ አስተዳደሩ ምክር ቤቱ በቆሼ በደረሰው አደጋ ለተጎዱ ዜጎች የገንዘብ ድጋፍ አደረገ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 11፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት በተለምዶ ቆሼ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በቆሻሻ ክምር መደርመስ አደጋ ለተጎዱ ዜጎች የገንዘብ ድጋፍ አድርጓል።

የምክር ቤቱ አፈ ጉባዔ ዶክተር ታቦር ገብረመድህን በዛሬው እለት አደጋው የደረሰበት ስፍራ በመሄድ የአደጋው ተጎጂዎችን እና በአደጋው ቤተሰቦቻቻውን ያጡትን ሰዎች አፅናንተዋል።

በጉብኝቱ ወቅትም ምክር ቤቱ በአደጋው የተጎዱ ሰዎችን በመደገፍ የበኩሉን ሀላፊነት እንደሚወጣ አስታውቀዋል።

ምክር ቤቱ በአደጋው የተጎዱ ሰዎችን መልሶ ለማቋቋም የሚውል የ500 ሺህ ብር የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉንም ነው አፈ ጉባኤው የገለጹት።

ከዚህ በተጨማሪም የአዲስ አበባ ከተማ ብድር እና ቁጠባ ተቋም 250 ሺህ ብር ድጋፍ ያደረገ ሲሆን፥ ቃለ ህይወት ቤተ ክርስቲያን 300 ሺህ ብር እንዲሁም ላሊበላ ወርቅ ቤት የ200 ሺህ ብር የገንዘብ ድጋፍ አድርገዋል።

በአጠቃላይ በዛሬው እለት የ1 ነጥብ 2 ሚሊየን ብር ድጋፍ ተደርጓል።

ከተለያዩ አካላት የገንዘብ ድጋፉን የተቀበሉት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ አባተ ስጦታው፥ ተጎጂዎችን በዘላቂነት ለማቋቋምና ህይወት እንዲቀጥል የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

በዛሬው እለት ከተለያዩ ተቋማት ለተደረገው የገንዘብ ድጋፍም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የዛሬውን የገንዘብ ድጋፍ ሳይጨምር እስካሁን ድረስ ቃል የተገባው እና በገንዘብ የተሰበሰበው ድጋፍም ከ65 ሚሊየን ብር ደርሷል።

እንዲሁም ከ2 ነጥብ 4 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት የቁሳቁስ ድጋፍ መደረጉን ከአዲስ አበባ ከተማ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

በተያያዘ ዜና ዳሽን ቢራ ፋብሪካ አክሲዮን ማህበር በአደጋው ህይወታቸውን ላጡ ቤተሰቦችና ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች ማቋቋሚያ የሚሆን የ1 ሚለየን ብር ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቋል።

በደመቀ ጌታቸው