ብሪታንያ በመጪው ረቡዕ ከህብረቱ የመውጣት ጉዞዋን ትጀምራለች

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 11፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የብሪታንያዋ ጠቅላይ ሚኒስትር ቴሬዛ ሜይ በመጪው ረቡዕ ሀገሪቱ ከአውሮፓ ህብረት መውጣቷን ለህብረቱ በይፋ ያሳውቃሉ ተባለ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ሜይ ለቀሪዎቹ 27 የህብረቱ አባል ሀገራትም ደብዳቤ ይፅፋሉ ብሏል ከጠቅላይ ሚኒስትሯ ቢሮ የወጣ መረጃ።

ከዚህም በተጨማሪ ከህብረቱ የመውጣት ድርድሩ በአጭር ጊዜ እንደሚጀመር ነው የተገለጸው።

የአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት የተፈራረሙት እና በ2009  ህግ የሆነው የሊዝበኑ ስምምነት አካል የሆነው አንቀፅ 50 መሰረት ማንኛውም አባል ሀገር ከህብረቱ ሲወጣ ለህብረቱ ኮሚቴ ማሳወቅ ይኖርበታል።

ከአባልነት የመውጣት ሂደቱንም ለሁለት አመት ያህል ድርድር በማድረግ ማጠናቀቅ እንደሚገባ አንቀፅ 50 ያዛል።

ከህብረቱ የመውጣት ድርድሩ በተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ ከተከናወነ ብሪታንያ ከህብረቱ አባልነቷ መጋቢት 2019 ላይ ሙሉ በሙሉ ትወጣለች።

ብሪታንያውያን ከዘጠኝ ወራት በፊት በተደረገ ህዝበ ውሳኔ 51 ነጥብ 9 ለ48 ነጥብ 1 በሆነ ድምፅ ከህብረቱ መውጣትን መምረጣቸው ይታወሳል።

 

ምንጭ፦ ቢቢሲ