ኢትዮ ቴሌኮም የሞባይል ኢንተርኔት ሲቋረጥ ያልተጠቀሙበትን ሂሳብ መጠቀም የሚያስችል አሰራር ተግባራዊ አደረገ

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 9 ፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮ ቴሌኮም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተከትሎ የሞባይል ዳታ ኢንተርኔት አገልግሎት ሲቋረጥ ደንበኞች ያልተጠቀሙበትን ሂሳብ መልሰው የሚጠቀሙበትንና የአገልግሎት መጠቀሚያ ጊዜውን ማራዘም የሚያስችል ስርዓት ተግባራዊ ማድረጉን አስታውቋል።

ደንበኞች ያልተጠቀሙበትን ቀሪ ሂሳብና የሚያበቃበትን የአገልግሎት ጊዜ ወደ *804# በመደወል ማወቅ የሚችሉበት ስርዓት መመቻቸቱን ኩባንያው ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ያደረሰው መረጃ ያመለክታል።

በዚህም መሰረት ለቅድመ ክፍያ፣ ለቢዝነስ ሞባይል ተጠቃሚዎች፣ ለድምጽና ዳታ ጥቅል አገልግሎት እንዲሁም ለገበታ ጥቅል እና የስጦታ አገልግሎት ደንበኞች የአገልግሎት መጠቀሚያ ጊዜን አራዝሟል።

ለሞባይል ድህረ ክፍያ ዳታ አገልግሎት የዳታ ብቻ አገልግሎት እና የጥቅል አገልግሎት ደንበኞች ያልተጠቀሙበትን ሂሳብ መልሰው በቀጣይ መጠቀም የሚችሉበት ሁኔታ ተመቻችቷል፡፡