የፊንጫ ስኳር ፋብሪካ አቋርጦት የነበረውን የኢታኖል ምርት አቅርቦት ዳግም ጀመረ

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 9 ፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) የፊንጫ ስኳር ፋብሪካ አቋርጦት የነበረውን የኢታኖል ምርት አቅርቦት ዳግም መጀመሩን የማዕድን ነዳጅና ተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር አስታወቀ።

ከፊንጫ በተጨማሪም የመተሃራ ስካር ፋብሪካንም ወደ ኢታኖል ማምረት ተግባሩ ዳግም ለመመለስ አጋጥሞ የነበረውን የቴክኒክ ብልሽት የመጠገን ተግባሩ በተኩረት እየተካሄደ ይገኛል ።

የማዕድን ነዳጅና ተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ባደረሰው መረጃ የፊንጫን ስኳር ፋብሪካ የኢታኖል ምርት ማቅረብ ተከትሎ፥ በአዲሰ አበባ ከሰኔ 2007 ዓ.ም አንስቶ ተቋርጦ የነበረው የኢታኖል ቤንዚን ደብልቅ አቅርቦት እንዲጀምር ተደርጓል።

በአሁኑ ወቅት ድብለቁ የተጀመረው በአምስት በመቶ ኢታኖል ሲሆን፥ ይህንን ወደ 10 በመቶ ለማሳደግ እቀድ ተይዞ እየተሰራ ይገኛል።

ድብልቁ በአምስት በመቶ ኢታኖል ሲጀመርም በአዲስ አበባ ብቻ በየወሩ 510 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ወጪን የሚያድን መሆኑን ሚኒስቴሩ አስታውቋል።