የሕወሃት ታጋዮችን መስዋዕትነት የአገሪቷን ህዳሴ በማረጋገጥ መመለስ ይገባል

አዲስ አበባ፣ የካቲት 10፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የህዝባዊ ወያነ ሃርነት ትግራይ /ሕወሃት/ ታጋዮች የከፈሉትን መስዋዕትነት የአገሪቷን ህዳሴ ለማረጋገጥ በመረባረብ መመለስ እንደሚገባ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ተናገሩ።

የኢህአዴግ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ሠራተኞች 42ኛውን የህወሃት ኢህአዴግ ምስረታ በዓል በተለያዩ ዝግጅቶች አክብረዋል።

የምክር ቤቱ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ አራቱን ብሄራዊ ድርጅቶች ወክለው የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የህወሃት የትጥቅ ትግል የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች የነጻነት፣ የእኩልነት፣ የፍትህና የማንነት ማረጋገጫ እሴትና ትሩፋት የተረጋገጠበት መሆኑንም በመልዕክታቸው ጠቅሰዋል።

"42 ሲቆጠር ቁጥር ነው፤ ነገር ግን በደም የተገነባ ትልቅ እሴት ያረጋገጡ፤ ፍትህ ዴሞክራሲና ሠላም የህዝቦች እሴት እንዲሆኑ ያደረጉ ውድ የመስዋዕትነት ውጤት ዓመታት ናቸው" ብለዋል።

ትግሉ አምባገነኑን የደርግ ስርዓት በማስወገድ የብሄር ብሄረሰቦች እኩልነት የተረጋገጠበት እንደነበር ያስታወሱት አቶ ሽፈራው ለተገኘው ድል የትግራይ ህዝብና ህወሃት ውድ ዋጋ መክፈላቸውን ተናግረዋል።

"የቀደሙት ታጋዮች ህዳሴዋ የተረጋገጠ ኢትዮጵያን ለመፍጠር መስዋዕት ሆነዋል" ያሉት አቶ ሽፈራው ታጋዮቹ የወደቁለትን ዓላማ ከግብ ለማድረስ ርብርብ ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ህዝብ ዋነኛ ጠላት ድህነት መሆኑን በመጥቀስም ድህነትን ለማስወገድ ከህወሃት የትግል ታሪክ በጽናት መታገልን መማር እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
የብአዴን ተወካይ አቶ እሸቴ አስፋው ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት ህዝቡ ከህወሃት የትግል ታሪክ ፅናትን፣ አንድነትንና ይቻላል ባይነትን መማር ይኖርበታል ብለዋል።

"ብአዴንና ህወሃት በደምና በአጥንት የተገነቡ፣ አንድ ዋጋ የከፈሉ ናቸው" ያሉት ተወካዩ ብአዴን ለኢትዮጵያ ህዳሴ ስኬት ከህወሃት ጋር ተባብሮ መስራቱን እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

ከህወሃት ኢህአዴግ የመጡት አቶ ይርጋለም መዓሾ በበኩላቸው የቀደሙት ታጋዮች የከፈሉት መስዋዕትነት አሁን ላለው ሠላም፣ ዕድገትና ዴሞክራሲ መሰረት መጣሉን ገልጸዋል።

ተተኪው ትውልድ የታጋዮችን አደራ በመረከብ ድህነትን ለማጥፋት የሚያደርገውን እንቅስቃሴ ማጠናከር አለበት ብለዋል።

"አሁን የትጥቅ ትግል ጊዜ አልፏል፤ ጊዜው የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት የአስተሳሰብ ትግል የሚደረግበት ነው" ሲሉም ተናግረዋል።

የኪራይ ሰብሳቢት አመለካከትን መመከት የሚያስችል የአስተሳሰብ ትግል ማድረግ እንደሚያስፈልግም አክለዋል።

በበዓሉ ላይ ለታጋይ ሰማዕታት የህሊና ጸሎትና የጧፍ ማብራት ስነ-ስርዓት የተካሄደ ሲሆን በዓሉን በአስመልክቶ ከህወሃት ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽህፈት ቤት የወጣ መግለጫም በንባብ ቀርቧል።

ምንጭ ፦ ኢዜአ