የወጣቶች የስራ እድል የመፍጠር ተግባር እንዲፋጠን ባለድርሻ አካላት እንዲረባረቡ ተጠየቀ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 10፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የወጣቶች ተዘዋዋሪ ፈንድን ተጠቅሞ ለወጣቱ የስራ እድል የመፍጠር ተግባር ሊፋጠን እንደሚገባ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን አሳሰቡ።

በተዘዋዋሪ ፈንዱ አጠቃቀም ዙሪያ ለባለድርሻ አካላት ዛሬ በአዳማ ከተማ በተዘጋጀው መድረክ ላይ የተገኙት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደተናገሩት ባለፉት ዓመታት የወጣቶችን ፓኬጅ መሰረት ያደረገ ሰፊ የልማት እንቅስቃሴ ሲደረግ ቢቆይም ፥የሚፈለገውን ያህል ወጣቱን ማርካት አልተቻለም ፡፡

የወጣቱን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የመንግስት ተቀዳሚ ተግባር ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ የወጣቶች ተዘዋዋሪ ፈንድ ለታለመለት ዓላማ በማዋል የልማቱ ተሳታፊና ተጠቃሚነታቸው እንዲረጋገጥ ባለደርሻ አካላት መረባረብ ይገባቸዋል ብለዋል።

የወጣቱን የሥራ አጥነት ችግር ለመፍታት ከዚህ ቀደም በነበረው አሰራር መሄድ የወጣቶችን ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት አይቻልም ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ካለፉት ደካማ ጎኖች በመነሳት በፍጥነት ወደ ተግባር ምዕራፍ መግባት ይኖርብናል ነው ያሉት ፡፡

ሁሉንም ስራ አጥ ወጣቶች ተጠቃሚ ማድረግ እንዲቻል በየደረጃው የመለየት፣ የማደረጃት፣ የክህሎትና ሙያዊ ስልጠና በመስጠት ወደ ተግባር መግባት እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

መንግስት ያመቻቸው የወጣቶች ተዘዋዋሪ ፈንድ ለተፈለገው ዓላማ እንዲውል በፌዴራልና በክልል ያሉ የወጣቶች አደረጃጀት ፣ ባንኮች፣ የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማትና ሌሎችም የባለድርሻ አካላት በአጠቃቀም መመሪያ ላይ ግልፅ ግንዛቤ ይዘው ወደ ተግባር እንዲገቡ መንግስት የበኩሉን ክትትልና ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታወቀዋል፡፡

በመላ ሃገሪቱ በተደረገ የስራ አጦች ምዝገባ እስከ አሁን 2 ነጥብ 9 ሚሊዮን በላይ የስራ አጥ ወጣቶችን በከተማና ገጠር ተለይተውና ተመዝግበው እንደሚገኙ የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትር አቶ ርስቱ ይርዳው ገልጸዋል።

በወጣቶች ተዘዋዋሪ ፈንድ አሰራር መመሪያና አጠቃቀም ላይ ከሁለቱ የከተማ መስተዳድሮችና ከዘጠኝ ክልሎች ከተወጣጡ የሚለከታቸው አካላት ጋር በአዳማ የተካሄደው መድረክ የዝግጅቱ አካል መሆኑን የተናገሩት ሚኒስትሩ ፥ ወጣቶችን ወደ ስራ ለማስገባት በክልሎች የተደራጀው ግብረ ሃይል እስከ ቀበሌ ድረስ በመውረድ ጠንካራ ድጋፍና ክትትል በማድረግ ወደ ተግባር መግባት እንዳለበትም አሳስበዋል።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከባለድርሻ አካላት ጋር በወጣቶች ተዘዋዋሪ ፈንድ አስተዳደር የአሰራር መመሪያ ላይ ውይይት ያካሄደ ሲሆን ፥የተለየቱንም ወጣቶች ለማደራጀት፣ ስልጠና ለመስጠት ፣ የስራ እቅድ ፣የመስሪያና መሸጫ ቦታ አቅርቦትና የተዘዋዋሪ ብድር አገልግሎቱ የተቀላጠፈ ለማድረግ ዝግጅት እየተጠናቀቀ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

የብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ተክለወልድ አጥናፍ በበኩላቸው የወጣቶች የስራ አጥነትን ቁጥር ለመቀነስ በፈጣን ዕድገት ውስጥ ተዋናይና ተጠቃሚ የሚሆኑበት አማራጮችን ማስፋት ወሳኝ መሆኑን የገለጹ ሲሆን ፥ ጎልቶ የወጣውን የስራ አጥነት ችግር ዘላቂ መፍትሄ እንዲያገኝ መንግስት በአዋጅና በመመሪያ የተደገፈ የህግ ማዕቀፍ መዘርጋቱን እና የሚቀረው ተጨባጭ ስራ ውስጥ መግባት ብቻ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

መንግስት ለወጣቶች ያመቻቸው ተዘዋዋሪ ፈንድ ተግባራዊ ለማድረግ እንዲቻል ከሦስት ሺህ 900 በላይ የንግድ ባንክ ቅርንጫፎችና አንድ ሺህ 700 የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት መዘጋጀታቸው ተገለጸ፡፡

በገጠርና በከተማ ከ18 እስከ 34 ዕድሜ ውስጥ የሚገኙ 18 ሺህ ቀበሌዎች ውስጥ ከ30 ሚሊዮን በላይ ወጣቶች መኖራቸውን የተናገሩት አቶ ተክለወልድ አዳዲስ የስራ አማራጮችን በማስፋፋት ተደራሽነታቸውን ማረጋገጥ እንደሚጠበቅም ጠቁመዋል።

የንግድ ባንኩ ፈንዱን ማስተዳደር ብቻ ሳይሆን በብድር አገልግሎቱ ላይ በሙሉ አቅሙ እንደሚሰራ ያረጋገጡት የባንኩ ገዢ፥ ባንኮችና የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ውስጥ ወጥነት ያለው አሰራር ተግባራዊ እንዲደረግ መመሪያው ያግዛል ብለዋል፡፡ 

ለአንድ ቀን በተዘጋጀው መድረክ ላይ የወጣቶች አደረጃጀቶች፣የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት፣ባንኮች፣የጥቃቅንና አነስተኛ ማይክሮ ኢንተርፕራይዝ ልማት ኤጄንሲዎች ፣ የወጣቶችና ስፖርት ቢሮ አመራሮች ተሳትፈዋል።

በታደሰ ብዙዓለም