የጥራት መጓደል እና የላኪዎች ተገቢ ያልሆነ ፉክክር የቡና ወጪ ንግድ አደጋ ሆነዋል

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 10 ፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) የጥራት መጓደል እና የቡና ላኪዎች ተገቢ ያልሆነ ፉክክር የኢትዮጵያ የቡና ወጪ ንግድ አደጋ ሆኗል እየተባለ ነው።

ለአለም ገበያ ከሚቀርበው ቡና 4 ነጥብ 2 በመቶውን የምታቀርበው ኢትዮጵያ፥ ጥራት እና ምርታማነት በዘርፉ ግብይት ዋና ፈተና ሆኖ ይነሳል።

ጥናቶች እንደሚያሳዩት ሀገሪቱ ከጠቅላላ አመታዊ የቡና ምርቷ ለወጪ ገበያ የምታቀርበው ከ40 በመቶ አይበልጥም።

ሃገሪቱ በ2000 ለውጪ ገበያ ካቀረበችው 126 ሺህ ቶን ቡና ከ344 ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ አግኝታለች።

ባለፈው አመት ለውጪ ገበያ ከቀረበው 183 ሺህ ቶን ቡና ደግሞ 780 ሚሊየን ዶላር ገቢ ተገኝቷል፤ ይሁን እንጅ ገቢው በአመቱ ለማግኘት ከታቀደው እጅጉን ያነሰ ሲሆን፥ ሀገሪቱ የቡና ወጪ ንግድ ገቢን አሳክታ አታውቅም።

ባለሃብቶች ደግሞ በዘርፉ በርካታ ችግሮች መኖራቸውን ያነሳሉ፤ በግብርና ምርቶች ማከማቻ መጋዘን በደረጃ ከገዙት በታች የሆነ ቡና እንደሚቀርብላቸው ይናገራሉ።

ከዚህ ባለፈም በኢትዮጵያ ምረት ገበያ ባለስልጣን ቡናውን ከአለም አቀፉ የቡና ዋጋ በበለጠ እንደሚገበያዩም ነው የሚናገሩት።

ቡና አቅራቢ እና ላኪዎቹ ቡና ችግር ላይ ነው የሚል ሃሳብም ይሰነዝራሉ፥ የውጪ ገዥዎችም ቡናው ተቀይሯል በሚል ከገበያ እየራቁ መሆኑን በማንሳት።

በቅርቡ የተቋቋመው የኢትዮጵያ የቡና እና ሻይ ግብይት እና ባለስልጣን በበኩሉ፥ ችግሮቹ መኖራቸውን አምኗል።

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳኒ ረዲ እንደሚሉትም፥ ድንገተኛ የጥራት ፍተሻ ለማድረግ እቅድ ተይዟል።

ከዚህ በኋላ ለውጪ ገበያ የቀረበ ቡና ደረጃ ሲወጣለት እና ሲመረመር፥ ቡና አቅራቢው፣ የመጋዘን ድርጅት እና የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባለስልጣን ባለሙያ በተገኙበት እንዲሆን ተወስኗል።

የቡና ናሙናውም ቡናው ውጪ ሀገር ተልኮ በገዢው ተቀባይነትን እስከሚያገኝ ድረስ እንዲቀመጥ ተደርጎ የጥራት ችግር ካለበት አቅራቢው የሚጠየቅበት ስርዓት መዘርጋቱንም ተናግረዋል።

ዋጋን በተመለከተም በምርት ገበያ ባለስልጣን በኩል በሚፈፀም ግብይት የቡና ዋጋ ከአለም ገበያ የመብለጡ መንስኤ፥ በላኪዎች መካካል በሚፈጠር ያልተገባ ውድድር የሚከሰት ነው ብለዋል።

ለዚህም ካሁን ቀደም ተነስቶ የነበረው የዕለታዊ ዋጋ ገደብ እንዲመለስ ማድረግን በመፍትሄነት መቀመጡን አንስተዋል።

በውሳኔው መሰረት የሀገር ውስጥ የቡና ዋጋ ከአለም የቡና ገበያ ዋጋ በአማካይ እንደሁኔታው አምስት በመቶ ዝቅ ወይም ከፍ እንዲል ይደረጋል።

በአለም ገበያ ያልተጠበቀ የዋጋ መውረድ ወይም መሰቀል ከተከሰተም የምርት ገበያ ባለስልጣን ቦርድ ሁኔታውን አይቶ እንዲወስን ይደረጋል ተብሏል።

 

 

 


በዳዊት መስፍን