የተመዘገበው ሰላምና መረጋጋት ሃገሪቱን የኢንቨስትመንት መዳረሻ አድርጓታል - መንግስት

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 10 ፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) የሃገሪቱ የኢንቨስትመንት ተመራጭነት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ገለጸ። 

ጽህፈት ቤቱ በሳምንታዊ መግለጫው ኢትዮጵያ የባለሃብቶችን ትኩረት እየሳበች መሆኗን ጠቅሶ፥ በበጀት አመቱ ስድስት ወራት ከውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት 1 ነጥብ 2 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር መመዝገቡንም ገልጿል።

በሃገሪቱ ከዘመናዊ የኢንዱስትሪ ፓርኮች መስፋፋት ጋር በተያያዘም በርካታ አለም አቀፍ ኩባንያዎች ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸውን አንስቷል።

ጽህፈት ቤቱ ሃገሪቱ አዋጭ የኢንቨስትመንት መዳረሻ እና ተመራጭ መሆኗም ለዚህ ምክንያት ነው ብሏል በሳምንታዊ የአቋም መግለጫው።

 

ይህ ስኬት በመላ ሃገሪቱ ያለው አስተማማኝ ሰላምና መረጋጋት እንዲሁም ሁኔታው ለባለሃብቶች ንብረት ዋስትና ያረጋገጠ ከመሆኑ አንጻር የመጣ እንደሆነም ጽህፈት ቤቱ አንስቷል።

ሃገሪቱ በፍጥነት እያደገ ያለ መሠረተ ልማት ማቅረብ መቻሏና፥ ለኢንቨስትመንት የተመቸ ሁኔታ መፍጠሯም እያደገ ላለው የውጭ ባለሃብቶች ተሳትፎ ምክንያት ነው ብሏል ጽህፈት ቤቱ።

ከዚህ ባለፈም የሃገር ውስጥ ባለሃብቶችም በሃገሪቱ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ተሳትፎ እያደረጉ መሆኑንም ጽህፈት ቤቱ በሳምንታዊ መግለጫው ጠቅሷል።

ጽህፈት ቤቱ በመግለጫው የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለዘለቄታው በመፍታት፥ ለሃገር ውስጥ እና የውጭ ባለሃብቶች የተሻለ የኢንቨስትመንት አማራጭ መሆናችንን እንቀጥላለንም ብሏል።