የመናውያን የሳዑዲ ዓረቢያን የአየር ጥቃት አወገዙ

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 10 ፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) የየመን ባለሥልጣናት በተሳሳተ የጦር አውሮፕላን ድብደባ ሳዑዲ ዓረቢያ በየመን ንጹሃን ዜጎች መገደላቸውን ተከትሎ ድርጊቱን አውግዘውታል፡፡

በአንድ ቤት የነበሩ ለቀስተኞች ለህልፈት መዳረጋቸውን ተከትሎ 9 ሴቶችና አንድ ህጻን የአውሮፕላኑ ሰለባ ሲሆኑ በርካቶችም ለተለያየ አካላዊ ጉዳት ተዳርገዋል፡፡

በሳዑዲ ጥምር ጦር ስር የሚተዳደረው የጦር አውሮፕላኑ በቅኝት ላይ እንደነበር ነው ከጥምር ጦሩ የተገኘው መረጃ የሚያሳየው።

በሰሜናዊ ሰንዓ አሺራ አደጋውን ያደረሰው አውሮፕላን በአንድ ጎሳ መሪ ቤት ለማስተዛዘን የተቀመጡ ሰዎችን ባልታሰበ የቦምብ ድብደባ ለህልፈት ዳርጓቸዋል፡፡

ጥምር ጦሩ በበኩሉ ሲቪሎች ላይ ጥቃት ለማድረስ አስቦ ሳይሆን ከየመን ጦር ባገኘሁት መረጃ መሰረት ነው ድብደባውን የፈጸምኩት ብሏል፡፡

ቦታው የየመን የጦር ሃይልና አማጺ ሃውቲዎች ከዚህ ቀደም ከፍተኛ ውጊያ ያደረጉበት ነው፡፡

የገልፍ አባል ሃገራት ጥምር ጦር ከዚህ ቀደም ባደረገው የአውሮፕላን ድብደባም 140 የየመን ለቀስተኞች መገደላቸው ይታወሳል፡፡

አሜሪካም ይህን ተከትሎ የማደርገውን ድጋፍ ላቋርጥ እችላለሁ ብላለች፡፡

በየመን የአየር ጥቃት ሰለባ ከምን ጊዜውም በላይ በጥምር ጦሩ በሚወሰደው እርምጃ እየጨመረ መሆኑ ተዘግቧል። 

የሰሩላህ የፖለቲካ ጉባኤ ባወጣው መግለጫ ሳዑዲ ዓረቢያ በሰሜን ሰንዓ ያካሄደችው የአየር ድብደባ ˝አሰቃቂ ወንጀል˝ ፈጽማለች በማለት ድርጊቱን አውግዟል፡፡

በዚህ ድርጊቷ ሳዑዲ ዓረቢያ በጦር ግንባር ጠንካራ አጸፋዊ ምላሽ እንደሚጠብቃት ጉባኤው በመግለጫው አስታውቋል፡፡

የየመን መንግስት ብሄራዊ መድህን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሃሺም ሸሪፍ ይህንኑ አስመልክተው ለተባበሩት መንግስታት ሁለት ደብዳቤዎችን በመጻፍ ድርጊቱ እንዲመረመርላቸው ጠይቀዋል፡፡

ምንጭ፦ ፕረስ ቲቪ እና ሬውተርስ