በደቡብ ክልል ለአደጋ ለተጋለጡ ከ458 ሺህ በላይ ዜጎች አስቸኳይ ድጋፍ እየተደረገ ነው

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 10 ፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ክልል በድርቅ ምክንያት ለአደጋ የተጋለጡ ከ458 ሺህ በላይ ዜጎችን በመለየት አስቸኳይ እርዳታና ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን የክልሉ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡

የጽህፈት ቤቱ ሃላፊ አቶ ሰለሞን ሀይሉ እንዳሉት፥ በክልሉ ደቡብ ኦሞ፣ ጋሞ ጎፋ ቆላማ አካባቢዎች እና በሰገን አካባቢ ህዝቦች ድርቅ ተከስቷል።

ሃላፊው በዞኖቹ ለሚገኙ ለ458 ሺህ 150 ዜጎች የእለት ደራሽ ምግብና ውሃ እየቀረበ መሆኑን ጠቅሰው፥ የቅርብ ክትትል የሚያስፈልጋቸው 180 ሺህ ዜጎች እየተረዱ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

በትምህርት ገበታ ላይ ለሚገኙ 124 ሺህ ተማሪዎች የምገባ ፕሮግራም እየተከናወነ መሆኑን የጠቀሱት ሃላፊው፥ በሁለተኛ ወሰነ ትምህርት ለ443 ሺህ ተማሪዎች የዕለት ምገባ ለማከናወን ዝግጅት ተጠናቋልም ብለዋል፡፡

ከዚህ ባለፈም በአካባቢው የሚገኙ 467 ሺህ 231 እንስሳትን ውሃና መኖ ወዳለበት ስፍራ እንዲንቀሳቀሱ መደረጉንም ገልጸዋል።

አያይዘውም ወደ ሌሎች ስፍራዎች መጓጓዝ ላልቻሉ እንስሳት፥ የመኖ ግዥ መፈጸሙንም ነው የገለጹት፤ 654 ሺህ ለሚሆኑት ክትባት መሰጠቱን በመጥቀስ።

በሌላ በኩል በክልሉ በኮንሶ ወረዳ በጸጥታ ችግር ምክንያት ተፈናቅለው ለነበሩ ነዋሪዎች የክልሉ መንግስት በመደበው 8 ሚሊየን ብር የማቋቋም ስራ እየተከናወነ መሆኑን አንስተዋል።

በጌዲኦ ዞን ለተፈናቀሉ ነዋሪዎች ደግሞ ከህብረተሰቡ በተሰበሰበ 7 ነጥብ 7 ሚሊየን ብር ድጋፍ ተደርጓልም ነው ያሉት።

የክልሉ መንግስት በመጀመሪያው ዙር 28 ሚሊየን ብር በመመደብ የማቋቋም ስራን እየሰራ መሆኑንም ሃላፊው አስታውሰዋል።

 

 


በሀይለኢየሱስ መኮንን