የኢትዮ - ሱዳን የድንበር ልማት ኮሚሽን ጉባኤ በመቀሌ እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 10 ፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያና ሱዳን በጋራ ጉዳዮቻቸው ላይ አብረው መስራታቸው በድንበር ላይ ለሚኖሩ የሁለቱ ሃገራት ሕዝቦች ግንኙነትና ሰላም መጎልበት አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑ ተጠቆመ።

የኢትዮ - ሱዳን የድንበር ልማት ኮሚሽን 18ኛ መደበኛ ጉባኤ ዛሬ በመቀሌ ሰማዕታት ሃውልት መሰብሰቢያ አዳራሽ ተጀምሯል።

በጉባኤው ላይ የትግራይ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አባይ ወልዱ፥ የኢትዮጵያና የሱዳን ሕዝቦች በቋንቋ፣ በታሪክ፣ በባህልና በተፈጥሮ ሃብት የተሳሰሩ ሕዝቦች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ለረዥም ዓመታት በጋራ ትብብርና በመተማመን ላይ የተመሰረተ ግንኙነት ያላቸው ወንድማማች ሕዝቦች መሆናቸውንም አስታውሰዋል።

ሃገራቱ በጋራ ለመልማትና ለማደግ ካላቸው ፍላጎት የተነሳ በተለያዩ የመሰረተ ልማት አውታሮች ለመተሳሰርና ችግሮቻቸውን በጋራ ለመፍታት እየሰሩ መሆኑንም ነው የተናገሩት።

አቶ አባይ እንዳሉት፣ ኢትዮጵያና ሱዳን ዲፕሎማሲያዊና ወንድማዊ ግንኙነታቸውን በማጠናከር በጋራ ጉዳዮቻቸው ላይ አብረው መስራታቸው በድንበር ላይ የሚኖሩ ሕዝቦቻቸው ግንኙነትና ሰላም በየጊዜው እየጎለበተ እንዲመጣ አድርጓል።

በቀጣይ ሃገራቱን በንግድ፣ በቱሪዝም ልማት፣ በጤናና በሌሎች ማህበራዊ ጉዳዮች ያላቸውን ግንኙነት ለማጠናከር ተጨማሪ ስራ መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ህገወጥ የሰዎች ዝውውር፣ ድንበር ላይ የሚካሄዱ የኮንትሮባንድ ንግድና የተፈጥሮ ሀብት ዘረፋን በመከላከል የሁለቱ ሃገራት ሕዝቦችን ጥቅም ለማረጋገጥ በጋራ መስራት እንደሚገባ አመልክተዋል።

በሱዳን የገዳሪፍ ክልል አስተዳዳሪና የልዑካን ቡዱኑ መሪ ሚስተር ማርቀኒ ሳልሕ ሰዒድ በበኩላቸው፣ ሁለቱም ሃገሮች ለሕዝቦቻቸው እድገትና ልማት በጋራ ተባብረው እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በድንበር በሚዋሰኑት አጎራባች ክልሎች የተጠናከረ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት እንዲኖራቸውና ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመግታት እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የኮንትሮባንድና ህገ ወጥ ንግድን ለመከላከል በጋራ ጥረት እየተደረገ ቢሆንም፣ የሃገራቱ የፖሊስና የፀጥታ አካላት ተባብረውና ጠንክረው እንዲሰሩ በማድረግ ህገ ወጥ ንግድንና የሰዎች ዝውውርን ለመግታት ተጨማሪ ጥረት ማድረግ እንደሚገባም አንስተዋል።

ለሁለት ቀናት በሚካሄደው ጉባኤ ሁለቱ ሃገሮች በሚዋሰኑባቸው ድንበሮች ያለውን የሰላምና ፀጥታ ጉዳይ፣ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ለማጠናከር እንዲሁም በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች የተከናወኑ ሥራዎች ይገመገማሉ፡፡

ጉባኤው በእስካሁኑ ሂደት የነበሩ ጠንካራና ደካማ ጎኖችን በመገምገም በቀጣይ መከናወን በሚገባቸው ሥራዎች ላይም እንደሚወያይ የኢዜአ ዘገባ ያመለክታል።